ቀጥታ፡

ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ምህዳርን ለማስፋት በተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ተገኝቷል

 

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ) ፦ ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ምህዳርን ከማስፋት ባለፈ በሙያዊ ብቃት እንዲጎለብቱ የአቅም ግንባታና የይዘት ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ገለጹ።

ባለፉት ዓመታት ለሕዝብ ትክክለኛና የተረጋገጠ መረጃ የሚያቀርቡ ጠንካራ መገናኛ ብዙሃንን ለማስፋት የአሰራር ማሻሻያዎችን ጨምሮ በመንግስት በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የበለጠ እንዲስፋፋና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምህዳሩ የበለጠ ክፍት፣ ተደራሽና ጠንካራ እንዲሆን መሰረት ተጥሏል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የተከናወኑ ስራዎች ተቋማቱ በዓይነት፣ በቁጥር፣ በተደራሽነትና በይዘት እንዲስፋፉ አስችሏል ብለዋል።

በተለይም ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የነበሩ የፈቃድ አሰጣጥ ማነቆዎችን በማሻሻል ወደ ዘርፉ መቀላቀል ለሚፈልጉ በርካታ ባለሙያዎችና ተቋማት ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

በዘርፉ የነበሩ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሻሻል፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሙያቸው በነፃነት እንዲሰሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም ተናግረዋል።

ሆኖም የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ከሙያዊ ኃላፊነትና ከሕግ ማክበር ጋር ተጣጥሞ መጓዝ እንዳለበት ገልጸው፤ ባለሙያዎች የሙያ ስነ-ምግባርን በመጠበቅ፣ የሀገሪቱን ሕግና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን በማክበር ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህ በኩል ሙያዊ ስነ-ምግባርን የሚጠብቁ፣ ለሕዝብ ትክክለኛና የተረጋገጠ መረጃ የሚያቀርቡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ከማፍራት አኳያ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ በቁጥርና በተደራሽነት ብቻ ሳይሆን፣ በሙያዊ ብቃትና በይዘት ጥራትም እንዲጠናከር የአቅም ግንባታና የይዘት ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል አማካኝነት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ መመረቃቸውን ገልጸዋል።

በዲጂታል ዘመን ፈተና እየሆነ የመጣው የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመቆጣጠርም ባለስልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የመገናኛ ብዙሃን ምህዳሩን ይበልጥ የሚያጠናክሩና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ፣ ጉዳዮችን በነፃና ሙያዊ በሆነ መልኩ እንዲያቀርቡና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም