ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመረዳዳትና ችግርን የመጋራት እሴትን እያጎለበተ ነው - ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ሆረታ

 

ሮቤ፤ ነሐሴ 09/2018 (ኢዜአ)፡- የበጎ ፈቃድ ሥራ እርስ በእርስ የመደጋገፍና ችግርን የመካፈል እሴትን እያጎለበተ ይገኛል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር የፊስካል ፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ሆረታ ተናገሩ።

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በባሌ ዞን ጎባ ወረዳ የችግኝ ተከላን ጨምሮ የተለያዩ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናወኑ።

የገንዘብ ሚኒስቴር የፊስካል ፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈቃዱ ሆረታ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች በአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በተያዘው ክረምትም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ለማከናወን ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በዚህም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣ የሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያና ወላጆቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሀገር ደረጃ እየተከናወኑ በሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እርስ በእርስ የመደጋገፍና ችግርን የመጋራት እሴትን እያጎለበተ መምጣቱን አመልክተዋል።

የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካባቢን በመጠበቅ ትውልድ ተሻጋሪ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ የትምህርት ቤት ግንባታና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉም የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።

ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን ያስታወሱት ደግሞ በሚኒስቴሩ የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ናቸው።

በዘንድሮ የክረምት ወቅትም በባሌ ዞን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነባው የሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ መከናወኑ የጥረቱ ማሳያ መሆኑን አክለዋል።

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው በዞኑ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በዘንድሮ ክረምት ወደ ዞኑ በመምጣት የሚያከናውኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችም የወገን አለኝታነታቸውን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

ድጋፉ የተደረገላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፉ ከችግሮቻቸው እንደሚያወጣቸው ገልጸው፤ የተቋማቱን አመራርና ሠራተኞችን አመስግነዋል።

በመርሃ ግብሩ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች፣ የዞኑ አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም