በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
ቁንቢ፤ ነሐሴ 09/2018 (ኢዜአ) ፦ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ በ640 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
በወረዳው ሀሮ ጉራቲ እና ሀሪሮ ቀበሌዎች የተገነቡትን ፕሮጀክቶች መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አመራር አባላት ናቸው።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢነርጂ ዘርፍ ከሚተገበሩ የልማት ተግባራት መካከል የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ሲሆን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክና ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክት ደግሞ በዚህ ፕሮግራም ስር ይከናወናል።
ከዋናው የብሔራዊ የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው በሚገኙ እንደ ቁምቢ ወረዳ ሃሮ ጉራቲ እና ሃሪሮ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች የሚዘረጉ የሶላር ሚኒ ግሪዶች ፣ ዘላቂና ንጹህ የሃይል አማራጭን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ የተነደፉ ናቸው።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በተለይም ቁምቢ ወረዳ እና አካባቢው በቆላማና በከፊል አርብቶ አደር አየር ንብረት ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረትና ተደጋጋሚ የድርቅ ስጋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው።
አሁን በእነዚህ ቀበሌዎች የተገነቡትን የውሃ እና የኢነርጂ ፕሮጀክቶች አጠናቆ ማስመረቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ትልቅ እርምጃ መሆኑ ነው የተገለጸው።
640 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶቹ 850 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸውና የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
ፕሮጀክቶቹ 3ሺህ 646 አባወራዎችን እንዲሁም የጤና፣ ትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
የወረዳው ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ ግንባታ የዘመናት የልማት ጥያቄያቸው በመመለሱ ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራር አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።