ቀጥታ፡

የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ አቅም እየሆነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 9/2018(ኢዜአ)፦ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ አቅም እየሆነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በ2019 የትምህርት ዘመን በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን በምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኤጀንሲው ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ከሚያከናውናቸው ሰው ተኮር ተግባራት መካከል የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በዋናነት ይጠቀሳል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብርን በትምህርት ቤቶች በመተግበር ከቅድመ አንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ (ቁርስና ምሳ) የሚመገቡበትን ሁኔታ ፈጥሯል።

ኢዜአ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ በ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርን ለማከናወን፣ ለተማሪዎች ዩኒፎርምና ደብተር ከማቅረብ አኳያ እያደረገ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተመለከተ አነጋግሯል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ አስተዳደሩ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሠራቸው ሰው ተኮር ሥራዎች መካከል የትውልድ ግንባታ ተግባራት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ትውልድን የማነጽ ተግባር ፍሬያማ እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን አንስተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በ2019 የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር እና የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት በጀት መመደቡን አስታውቀዋል።

በ2019 የትምህርት ዘመን ከ1 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ከ993 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ ከ1 ሚሊዮን 210 ሺህ በላይ ተማሪዎች ዩኒፎርም እና ደብተር ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል።

ኤጀንሲው በሚቀጥለው ዓመት የሚከናወነውን የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለተማሪዎቹ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ የሚያስችል የግብዓት አቅርቦት ትስስር የመፍጠር ሥራ በልዩ ትኩረት እየተሠራበት መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ትልቅ አቅም መፍጠሩንም ነው የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ የገለጹት።

መርሃ ግብሩ በተለይም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እንዲሁም የወላጆችን ኢኮኖሚያዊ ጫና እያቃለለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም