በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ባህርዳር ፤ነሀሴ 9/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
23ተኛው የአማራ ክልል ትምህርታዊ ክልላዊ ልማት ትብብር ፎረም የውይይት መድረክ በባህር ዳር እየተካሄደ ይገኛል።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ መኳንንት አደመ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የትምህርት ስራ ሀገርንና ትውልድን በዘላቂነት የመገንባት እና የማነፅ ስራ ነው።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከሰቱ ችግሮች በመማር ማስተማር ስራው ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ በተሰራ ስራ በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል ።
በዚህም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ይህንኑ በማጠናከር በ2019 የትምህርት ዘመን 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚልቁ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የመማር ማስተማር ስራ የሁሉንም ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትምህርት ዘመኑ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ስኬታማ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የቢሮው እቅድና በጀት ግምገማና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዘመነ አበጀ በመድረኩ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት በ2018 የትምህርት ዘመን 1 ሺህ 113 የትምህርት ተቋማትን በተሻለ ደረጃ መልሶ የመገንባትና የመጠገን ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በትምህርት ቤት ምገባም ከ650 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ በበኩላቸው ማህበረሰቡን በማሳተፋ የመማር ማስተማር ስራውን በተሻለ ቅንጅት እና ትብብር ለውጤት የሚያበቁ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ለዚህም ባለድርሻ አካላት እያደረጉት ያለው ድጋፋ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉን ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ስኬታማ ለማድረግ ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አቢዮት አሸናፊ ናቸው።
በመድረኩ በትምህርት ዘርፍ እየሰሩ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሀላፊዎችና አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።