ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።

የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ እንደገለጹት፤ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት አልምቶ በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል።


 

በተለይም በመደመር መንግስት ቱሪዝም ከዋና የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንዱ ሆኖ መወሰዱና ትኩረት መሰጠቱ ዘላቂነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከማልማት ባሻገር ነባር ቅርሶችን በመጠገንና በመንከባከብ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በጁገል አለም አቀፍ ቅርስ እድሳትን ጨምሮ ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎችና መሰል ተግባራት የክልሉ ቱሪዝም በፍጥነት እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።


 

በተጨማሪም በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 14700 የውጭ ሀገራት ና 180,754 የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የመስህብ ሃብቶችን ጎብኝተዋል ብለዋል።

በክልሉ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ202589 በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ 16500 በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የክልሉን የመስህብ ሃብቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም