ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እና የኢፌዲሪ ሚሲዮኖች በጋራ በጋሞ ዞን በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 40 ቤቶችን ለማጠናቀቅ ርክክብ ተደረገ

አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 9/2018(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እና የኢፌዴሪ ሚሲዮኖች በጋሞ ዞን በነበረው የመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን ለማገዝ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉ ቀደም ሲል በዞኑ ተከስቶ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ 40 ቤቶችን ለማጠናቀቅ የሚውል መሆኑ ተመላክቷል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

«በችግር ጊዜ የምናሳየውን ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን በማጠናከር፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍና አብሮ የመቆም ባህላችንን በማሳደግ ለትውልድ ማስረከብ ይጠበቅብናል» ብለዋል።

በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን በቋሚነት ለማቋቋም በተዘጋጀው ስፍራ በግንባታ ላይ የሚገኙ 40 የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ በዛሬው ዕለት የገንዘብ ድጋፍ ርክክብ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ለሴቶችና ሕፃናት አልባሳትና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በዞኑ ተከስቶ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ከአደጋ ስጋት ቀጠና ውጪ በሆነ ቦታ በብርብር ከተማ አስተዳደር ደልቦ ቀበሌ በሞዴል የገጠር መንደር በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።


 

በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችን በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ አስፈላጊ የሰብዓዊ ድጋፎች ከማድረግ ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት 100 ሞዴል የገጠር መንደር ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።


 

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በጋሞ ዞን በየካቲትና መጋቢት 2018 ዓም በጋጮ ባባ እና ሌሎች ወረዳዎች በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም