በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚገነባው የመማሪያ ክፍል ለታዳጊ ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል -የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚገነባው የመማሪያ ክፍል ለታዳጊ ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል -የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ
ባሕር ዳር፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚገነባው የመማሪያ ክፍል ለታዳጊ ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ገለጹ።
ኢዜአ በባሕር ዳር ከተማ ምስራቀ ፀሐይ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት የሕንፃ ግንባታ በዛሬው ዕለት አስጀምሯል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ቢዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኢዜአ የሚገነባው የመማሪያ ክፍል ለታዳጊ ሕፃናት ተማሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
ለትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም ጥራትን ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረትም አጋዥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በምስራቀ ፀሐይ ትምህርት ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት አስተባባሪ መምህርት አያል እምቢያለ፤ በአሁኑ ወቅት በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 150 ተማሪዎች እንደሚማሩ አስታውሰዋል።
አዲሱ የመማሪያ ሕንፃ ግንባታ ይህንን የተማሪዎች የክፍል ጥምርታ በማስተካከል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምንይችል ዓለማየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ በገጽታ ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም የጋራና አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ከሀገራዊ ተልዕኮው ባሻገር በማኅበራዊ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይም ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሠረት በባሕር ዳር ከተማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ማስጀመሩን ጠቅሰው፤ ግንባታው በጥራትና በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማት ግንባታ የትውልድ ግንባታ ዋነኛ መሠረት መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ኢዜአ ከመደበኛ ተግባሩ ባለፈ በጎ ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝ የችግኝ ተከላ የተከናወነ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግም ከወጣቶች ጋር የፓናል ውይይት ተካሂዷል።