ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን በዘንድሮው ክረምት በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ የቡና ችግኝ ተተክሏል

አዶላ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዘንድሮው ክረምት በ16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች መተከላቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጉጂ ዞን በምርጥ መዓዛው እና ጣዕሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጡ ልዩ የቡና ዓይነቶች መካከል አንዱ የሚገኝበት አካባቢ ነው።

የምድር ለምነት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና የደጋ አየር ጸባይ ዞኑ በቡና ልማት ተራጭቶ እንዲታወቅ አድርጎታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች የምርት ጥራት እና መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር ወጥተው ሳይንሳዊ ዘዴዎችን እንዲከተሉ ሲደረግ ቆይቷል።

በዘንድሮው ክረምት በዞኑ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሩን ከዘልማድ አሠራር አውጥቶ በተሻሻሉ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና በሽታን በሚቋቋሙ አዳዲስ የቡና ዝርያዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ የችግኝ ተከላና የልማት እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።


 

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በዞኑ በዘንድሮ ክረምት የቡና ልማቱን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ከ72 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የቡና ችግኞች እስካሁን በ16 ሺህ 233 ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ ዝርያ ድርቅና በሽታን በመቋቋም ከአንድ ሄክታር እስከ 18 ኩንታል ምርት ለመስጠት የሚያስችል አቅም ያለው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይህም ከነባሩ ዝርያ የሚገኘውን ከ7 ኩንታል በታች ምርት ከሁለት እጥፍ በላይ በማሳደግ አምራቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በ12 ወረዳዎች እስካሁን የተተከለው የቡና ችግኝ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ13 ሚሊዮን ገደማ ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በልማቱም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ54 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ ንግድ ጽሕፈት ቤት ቤቱ ሃላፊ አቶ አሬሩ ዋሬ ከዞኑ በተሻሻለ ዝርያ እየተስፋፋ የመጣው የቡና ልማት፣ ምርቱን በብዛትም ሆነ በጥራት እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ከዞኑ ከ231 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ለገበያ መቅረቡን ለአብነት አንስተዋል።


 

ምርቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱ ልማቱን ይበልጥ ለማስፋት ትልቅ የሥራ መነሣሣት መፍጠሩንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሀገር አቀፍ የምርምር ማዕከላት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሚገኙ በርካታ የእሼትና የደረቅ ቡና ኢንዱስትሪዎች ምርቱን በብዛትና በጥራት እያዘጋጁ ለገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው፤ የዞኑን የቡና ልማት ይበልጥ ለማስፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም