የዲጅታል ሚዲያ አማራጮችን ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጅታል ሚዲያ አማራጮችን ለጋራ ትርክት ግንባታ ለማዋል ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ዲላ ፤ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ )፡- የዲጅታል ሚዲያ አማራጮችን ለጋራ ትርክት ግንባታ፣ ለሀገር ልማትና በጎ ተግባራት ለማዋል በመትጋት ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስገነዘበ።
ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም ለወጣቶች በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም፣ በጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን የመከላከል እንዲሁም በሐቅ ማጣራት ዙሪያ በዲላ ከተማ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምስራቅ ጌቱ፤ በተለይም ወጣቶች የዲጂታል ሚዲያን ለልማትና ለሀገር ግንባታ በማዋል ለሁሉም የምትመች ሀገር በጋራ ለመገንባት አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
በዲጂታል ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛት፣ እውነታና ሀቅ ማጣራት ተገቢ መሆኑን አንስተው፤ አፍራሽና ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የግል ጥቅማቸውን አስበው የሚሰሩ እንዳሉ አንስተዋል።
በመሆኑም የዲጅታል ሚዲያ አማራጮችን ለጋራ ትርክት ግንባታ ለሀገር ልማትና በጎ ተግባራት ለማዋል በመትጋት ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚባ አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያና አመራር አንዲሁም ተጽኖ ፈጣሪ ወጣቶች ለዘላቂ ሰላምና ልማት አሻራቸውን ለማኖር እንዲተጉ ጠይቀዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ፤ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በብዛት ለጥላቻ ንግግር እና ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የተጋለጡ በመሆናቸው ሃቅን በማጣራት ለትክክለኛ መረጃ ስርጭት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያን ጅምር ስራዎች በማጠናከር ለሀገር ልማት መስራትና ለእውነት መትጋት በተለይም ከወጣቶች ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።