ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናክር ትልቅ መድረክ ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 9/2018 (ኢዜአ)፦ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናክር ትልቅ መድረክ ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ናቸው።

ኢዜአ ካነጋገራቸው ተመካካሪዎች መካከል ተስፋዬ ደጀኔ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ምክክሩ ለቆዩ ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ ያስቻለ አዲስ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጨምረው አመላክተዋል፡፡

በምክክሩ በርካታ ትምህርቶች የተወሰዱ ሲሆን፣ ለነበሩ ችግሮችም በርካታ የመፍትሔ ሀሳቦች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ ወደ ትልቅ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው ብለዋል፡፡


 

ሌላኛው ተመካካሪ ኢብሳ ኢብራሒም በበኩላቸው የምክክር መድረኩ ሂደት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውና አዎንታዊ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምክክሩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በስፋት ያሳተፈ በመሆኑ ሂደቱ የተሟላ እና አካታች መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ቦጋለ ሰይዳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም