በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእንስሳት ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ጂንካ፤ነሐሴ 9/2018(ኢዜአ):- የእንስሳት ሃብት ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከልና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን የቀይ አፈር-የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ግንባታ በመገባደድ ላይ ሲሆን በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሏል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና ንግድና ገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ አብርሃም፤ በክልሉ ያለው ሰፊ የእንስሳት ሃብት ልማት ለዜጎች የተሻለ ጥቅም እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በእንስሳት ሃብት ላይ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ንግድ ለመከላከልና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
የቁም እንስሳትን ወደ ግብይት ማዕከላት በማቅረብ በተሻለ ዋጋ ለማህበራትና ለዩኒየኖች ለማቅረብ የሚያስችል አሰራር ስለመዘርጋቱ አንስተዋል።
በኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከላት አማካኝነት በሀገሪቱ ለሚገኙ የኤክስፖርት ቄራዎች ዩኒየኖች በቀጥታ የሚያቀርቡበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር አደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ስዩም መታፈሪያ (ዶ/ር)፤ የእንስሳት ሀብት በብዛት በሚገኝባቸው የክልሉ አካባቢዎች የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት የኤክስፖርት ስታንዳርዱን የጠበቁ እንስሳትን ማቅረብ በሚያስችል መልኩ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የኤክስፖርት ቄራዎችን እና የተቀባይ አገራትን ፍላጎት ያማከለ የቁም እንስሳት በብዛትና በጥራት በማቅረብ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቱርሚ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀማ አይኬ፤ በከተማ አስተዳደሩ የተገነባው የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በተለይም አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የቁም እንስሳት ንግድ ህጋዊ ስርአቱን የተከተለ ሲሆን የመንግስት የገቢ ምንጭ እንደሚሆንና በከተማው ለሚገነቡ መሰረተ ልማቶች መሳለጥም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀው የኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከል ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም የምታገኝበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ታውቋል።