ቀጥታ፡

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ለማንኛውም ጥቃት ፈጣን ምላሽ ሰጪና ስጋቶችን አስቀድሞ መከላከል የሚችል የመላ ሠራዊቱ ሞዴል ኃይል ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ) ፦ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በተለየ ወታደራዊ ጥበብ በፍጥነት ፈጣን ምላሽ ሰጪና አስቀድሞ ስጋቶችን መከላከል የሚችል የመከላከያ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ መቺ ሀይል ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡

ኢታማዦር ሹሙ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ስለወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ለሠራዊቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ አድርጋ ገና ሳትረጋጋ ባንዳዎች ባደረሱባት ጥቃት ሀገር በተፈተነችበት ወቅት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሠራዊት የተደቀነውን አደጋ በመቀልበስ ረገድ ከባድ የተጋድሎ አድርጓል ሲሉም በበመድረኩ ላይ ገልጸዋል። 

በዚህም ምክንያት የውጊያ ማርሽ ቀያሪ የምድር ድሮን የሚል ስያሜ የተሰጠው ልዩ ሀይል መሆኑን በማብራራት ይህ ዕዝ አስካሁን ለሀገር ለከፈለው ዋጋ ኢትዮጵያ እንደምታከብረውና ነገም ይህንኑ ልዩ ብቃቱን ይዞ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ሠራዊቱ መስዋዕትነት የከፈለውና እየከፈለ የሚገኘው ሀገርን ለማሻገር መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ሠራዊቱን ሀገርን ከውጭ ጠላት ከመከላከል ባለፈ፣ የውስጥ ሰላምን በማጽናት ህልውናችን ተጠብቆ ዕድገት እንዲቀጥል የሚያስችል የዜጎች ክብር መገለጫ  አድርጎታል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ሻዕቢያ ከጅምሩ ኢትዮጵያን ከባሕር በር ለማራቅ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ፅምዶ ፈጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ደባ የሰራ ሃይል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ሕገ-ወጡ ህወሓትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሸጠና ለ27 ዓመታት ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ አጠንክሮ የሰራ ቅጥረኛ የገዛ ሀገሩን ሠራዊት ያጠቃ የክህደት ሃይል ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሕወሃት ክህደት የተፈተነች ነገር ግን ፀንታ የቆመች የልዩ ዘመቻ ሠራዊት መሰል ጠንካራ አርበኛ ልጆች ያሏት ሀገር ስለሆነች ጉዞዋን ቀጥላለች ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ፅንፈኞቹን የጥፋት ሃይሎች በባዕዳን ስትራቴጂ ሥር ተሰልፈው ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ፅምዶ የተባለ ጥምረት ቀርፀው ሕዝባችንን ለስቃይና መከራ በመዳረግ ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጓጉተው ቢሠሩም ይህ ፍላጎታቸው መቼም ሊሳካ አይችልም ብለዋል።

ህወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል እርስ በርሱ እንዳይተማመን  ሲሰራ የኖረ እኩይ ፖለቲካ አራማጅ ፀረ-ሀገር ሃይል ነው ብለዋል። 

ዛሬ ሴራው ከሽፎ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን መሰሪ ቡድን መጥፎ ተግባር ተርድቷል ብለዋል።

አሁን ላይ ህወሃት ለሻዕቢያ እየተላላከና የቀድሞ ጠላቶቹን ጽንፈኛ ሸኔንና ፅንፈኛ ፋኖን አቅፎ  የትላንት ክህደቱን በአደባባይ እየደገመው ይገኛልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በጀመረችው እድገትና ብልፅግና ወደፊት ትቀጥላለች፤ የታሪካዊ ጠላቶቿ ህልም አይሳካም ሲሉም ገልጸዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በአሁኑ ወቅት በትጥቅም በሰው ሀይል ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስታወስ ለሰፈር ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አቅጣጫ በሀገር ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በአስተማማኝ ዝግጁነት ላይ መሆኑን  ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም