ወጣቶችን በክህሎትና በአመለካከት ብቁ በማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶችን በክህሎትና በአመለካከት ብቁ በማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል
ሐዋሳ፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ወጣቶችን በክህሎትና በአመለካከት ብቁ በማድረግ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት መቻሉን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ለወጣቶች ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም ''SEED'' በሲዳማ ክልል የሦስት ዓመት የሥራ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡
የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረጽዮን አበበ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ወጣቶችን በክህሎትና በአመለካከት በማብቃት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ክህሎት መር ባለመሆኑ የተነሳ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ውጤታማ አለመሆን የዘርፉ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዘርፉ በዜጎች ክህሎትና አመለካከት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንደ ሀገር አቅጣጫ ተይዞ መሥራት ከተጀመረ በኋላ፤ በተለይ ወጣቶች በተሻለ አቅምና ፍላጎት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ውጤታማ የሆኑና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የቢሮው ምክትልና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ከበደ በበኩላቸው፤ አጋር አካላትን ከሥልጠና ተቋማት ጋር በማቀናጀት የክህሎት ክፍተቶችን የመሙላት እና ወደ ሥራ የሚገቡትን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅድሚያ ለክህሎትና አመለካከት በመስጠት የፋይናንስ፣ እንዲሁም የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎችን የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲቲዩት የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች አስተባባሪ አቶ ጌትነት ሳሙኤል፤ በኢንስቲትዩቱ የሚመራው የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም በአምስት ዓመታት ውስጥ ለ1 ሚሊዮን ወጣቶች ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አለው ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ ከተመረጡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመሆን የክህሎት ሥልጠና የመስጠት፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
በፕሮግራሙ በሲዳማ ክልል በሦስት ዓመታት ውስጥ ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶች የክህሎት ሥልጠና ያገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑት የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው አብራርተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመቀናጀትም ለኢንተርፕራይዞች ከ181 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንደተሰራጨ ጠቁመዋል፡፡
በፕሮግራሙ ድጋፍ ካገኙ ኢንተርፕራይዞች መካከል የጠይም ጋርመንት አባል የሆነችው ወጣት ቤርሳቤህ አለማየሁ እና የጃዋታ ጨርቃ ጨርቅ ማኅበር አባል የሆነችው ወጣት ራህመት ሁሴን፤ በፕሮግራሙ ባገኙት ሥልጠና ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የሂሳብ አያያዝና ሌሎች ክፍተቶች በመሙላት በሥራቸው ትርፋማ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል፡፡