የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚወስዱበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚወስዱበት ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚወስዱበት መሆኑን በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ሕብረት የሳህራዊ ሪፐብሊክ አምባሳደር ላሚን ባአሊ ገለጹ።
አምባሳደር ባአሊ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች ስኬታማ ጉዞ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ስኬታማ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄዷንም አንስተዋል።
ይህ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ዜጎች የፖለቲካ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ አዎንታዊ ማረጋገጫ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃት መሳተፋቸውን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ በጎ እርምጃ መሆኑንም አምባሳደር ባአሊ አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የሪፎርም አጀንዳ በሀገሪቱ ውስጥ ለበለጠ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚከናወኑ የተለያዩ የልማትና የለውጥ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤት እያመጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የዜጎችን ኑሮ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ጨምረው አንስተዋል፡፡
ይህ በኢትዮጵያ እውን እየሆነ ያለው ውጤታማ ሪፎርም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረትና እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህ የኢትዮጵያ ስኬታማ ተሞክሮ በአጠቃላይ በአፍሪካ ደረጃ የሚገኙ ሌሎች ሀገራት ትምህርት ሊወስዱበት የሚችል ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ የፖለቲካ ልምምድ እንደሆነ የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ እየተደረገ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ለሁሉም አካላት ዘላቂ ጥቅም ለማስገኘት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሳህራዊ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መካከል እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የነበረውን ትብብር አውስተው፣ የሀገራቱ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።
ባህል፣ ስፖርት፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ጤና እና ሌሎች የጋራ ፍላጎት በሆኑ ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብሩን የበለጠ ለማስፋት እንደሚሰራም አምባሳደር ላሚን ባአሊ ገልጸዋል።