በከተሞች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ እየታዩ ያሉ ለውጦች በዘርፉ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እየተገነባ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ እየታዩ ያሉ ለውጦች በዘርፉ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እየተገነባ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው
አዳማ ፤ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ )፡- በከተሞች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ እየታዩ ያሉ ለውጦች በዘርፉ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እየተገነባ ለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ።
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በአዳማ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎችን ገብኝቷል።
በዚህ ወቅት አቶ ጥራቱ በየነ እንደገለጹት፤ በከተሞች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ እየታዩ ያሉ ለውጦች በዘርፉ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እየተገነባ ለመሆኑ ማሳያ ናቸው።
"ከዚህ ቀደም ልምድ ለመቅሰም ወደ ውጭ ሀገር ከተሞች እንሄድ ነበር፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በሀገር ውስጥ ከተሞች ከቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀም፣ ከአገልግሎት ዲጂታላይዜሽንና መሠረተ ልማት ዝርጋታ አንጻር ልምድና ዕውቀት መቅሰም እየቻልን ነው" ብለዋል።
በተለይ በአዳማ ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን እና የጸጥታና ደኅንነት አሠራሮችን ዘመናዊ ከማድረግ አኳያ የተሰሩ ሥራዎች ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድባቸው እንደሁኑ ገልጸዋል።
በተመሳሳይም በትራንስፖርት ስምሪትና በትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት፣ ቴክኖሎጂን በማላመድና አገልግሎት ላይ በስፋት በማዋል ረገድ ጥሩ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በተለይ የመሬት ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደርና ለሕዝብ ልማት በማዋል ረገድ የአዳማ ከተማ አስተዳደር የመሬት ካዳስተር ሥርዓት በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በከተማ ግብርና፣ የአርሶ አደሩን ሕይወትና የአኗኗር ዘይቤ ለማዘመንና ከተማዋ አርሶ አደሩን በማቀፍ ዕድገቷ እንዲቀጥል የአርሶ አደሮች ሞዴል መንደር ልምድ የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም አርሶ አደሩ የተሟላ መሠረተ ልማት በአንድ ቦታ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም ከአዳማ ከተማ የተገኘውን ተሞክሮ በከተማቸው ካለው አተገባበር ጋር በማቀናጀት ወደ ውጤት እንደሚቀይሩትም ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው፤ በከተማዋ በተከናወነው የመሠረተ ልማት ዝርጋታና አገልግሎትን በማዘመናችን አዳማ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን ሰፊ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ መቻሉንም ገልጸዋል።
በአዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ለማዘመን የተሠራው ሥራ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም የመሬት ሀብቱን በአግባቡ በማስተዳደር ከሌብነትና ምዝበራ መታደግ መቻሉን፣ የከተማዋ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን፣ ሕዝቡ በከተማዋ ልማት እያደረገ ያለው ተሳትፎ እንዲጨምርና እንዲጠናከር ማስቻሉንም ጠቁመዋል።