በድሬዳዋ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማኅበራዊ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማኅበራዊ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ድሬደዋ ፣ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለትምህርት ቤቶችና ማኅበራዊ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመላከተ።
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችን ለግሷል፤ በመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ የድሬዳዋ ማዕከልም ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር አከናውኗል።
በወቅቱም የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ እንደተናገሩት፤ ቢሮው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመሳተፍ ባሻገር በሁሉም የገጠርና የከተማ ወረዳዎች በሚገኙ አደባባዮች ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ነፃ ምርመራና ሕክምና እየሰጠ ይገኛል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠርና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በአንድነት መፍታት እንደሚቻል እያረጋገጠ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቢሮው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችን የለገሰ ሲሆን፤ ለመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ የድሬዳዋ ማዕከልም ማዕድ ማጋራቱን ተናግረዋል።
ቢሮው ከለገሳቸው የመማሪያ ቁሳቁስ በተጨማሪ ከቢሮው ሠራተኞች የተሰበሰቡ በርካታ አልባሳትን ለመቄዶንያ የድሬዳዋ ማዕከል መለገሱንም ገልጸዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ባህልን በማጠናከር ማኅበራዊ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ተቋማዊ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የሴክተርና የግል ተቋማት የተለያዩ የትምህርት መማሪያ ግብዓቶችን እየደገፉ መሆኑን አንስተዋል።
ድጋፉን በማጠናከር አንድም ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ሕፃን ከትምህርት ገበታው እንዳይለይ በማድረግ የነገዋን ታላቅ ሀገር መገንባት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አስምረውበታል።
ዛሬ የጤና ቢሮ ያደረገው ድጋፍም የመረዳዳት እሴቱ መጠናከር ማሳያ መሆኑን ገልጸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።