ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የመመካከር ባህልን በማዳበር ሀገራዊ መግባባትን እያጠናከረ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ)፦ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ የመመካከር ባህልን በማዳበር ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናክር መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ናቸው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በህዝቦች መካከል የማይናወጥ ወዳጅነትን ለመገንባት እና በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባች ሀገርን ለማስቀጠል ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ እሸቱ ኤራቦ እንዳሉት፤ የምከክር ጉባኤው ለዘመናት ማህበረሰቡ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች መፍትሄ ለመስጠት ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ለማድረስ የሚያሰችል ነው።

ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች፣ የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለማስረከብ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።


 

አቶ ባንቲሁን ትዛዙ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ ባህላዊ የእርቅና የመመካከር እሴት እንዲያንሰራራ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክክሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት የመጡ ማህበረሰቦችን በአንድ ጥላ ስር በማገናኘት የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ትስስር ለማጠናከር ማስቻሉን አብራርተዋል።

ሀሳቦችን በነጻነት ወደ መድረክ ማምጣትና በግልጽነት መነጋገር ለዘላቂ ሰላምና ግንባታ ትልቅ መሰረት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር ናቸው።


 

ተመካካሪዎቹ በሰፊ የቡድን ውይይቶች ያነሷቸው ነጥቦች ሀገራዊ አጀንዳዎችን በስፋትና በጥልቀት ያቀፉ በመሆናቸው፣ ሂደቱ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም