የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አካታችና አሳታፊነት ሀገራዊ መግባባትን መገንባት ለሚሹ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተመራጭ መንገድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አካታችና አሳታፊነት ሀገራዊ መግባባትን መገንባት ለሚሹ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተመራጭ መንገድ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አካታችና አሳታፊነት አቀራረብ ሀገራዊ መግባባትን መገንባት ለሚሹ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተመራጭ መንገድ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ያሲን አሕመድ ገለጹ።
የኢንስቲትዩቱ ፕሬዚዳንት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በፖለቲካ መሪዎችና በመንግሥት መካከል ከሚደረጉ ምክክሮች በተለየ ወደ ሕዝብ በመውረድ ከታች ወደ ላይ የመጣ ሂደት ነው።
በአፍሪካ በርካታ ሀገራት የሚካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች የሕዝብን ስጋትና ምኞት በማያንጸባርቅ መልኩ በመሪዎች ደረጃ በሚደረሱ ስምምነቶች ተጀምሮ ለሕዝብ የሚቀርቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ ግን ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ የሕዝብ ተሳትፎንና አካታችነትን በማረጋገጥ ወደ ብሔራዊ ደረጃ የሚሸጋገር ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ጉባኤው የታደሙ የተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ስብጥርና ተሳትፎም የምክክሩን አሳታፊና አካታችነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤውም የዜጎችን ስጋቶችና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ዐበይት አጀንዳዎች በመለየት ወደ ብሔራዊ አጀንዳ ለማምጣት ያለመ ወሳኝ መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም በዘመናዊት ኢትዮጵያ የሀገር ግንባታ ሂደትና ታሪክ ውስጥ ሁሉንም ዜጎች ማዕከል በማድረግ በተቋማዊና ፖለቲካዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መቀራረብን የሚገነባ አቀራረብ መሆኑን አስረድተዋል።
የምክክር ጉባኤው ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላትን ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን የዘመናት ውስብስብ ጉዳዮች በሰለጠነ የምክክር መድረክ ለመመልከትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
በሰለጠነ ዓለም ውስጥ የትጥቅ ትግል ቁርሾንና መቃቃርን የሚያባብስ እንጂ ሰላምን የሚያመጣ አይደለም ያሉት ያሲን አሕመድ፤ በመርህ ላይ የተመሠረተ ምክክር ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአመፅና አዋኪ የትጥቅ ትግል ሀገርን በማጎሳቆል የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት፣ የዕድገትና የልማት ፍላጎት ከማቀጨጭ ያለፈ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አካታችና አሳታፊ የምክክር ጉባኤም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማጎልበት በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመገንባት እንደሚረዳ አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ በፓርላማ በጸደቀ ሕግ መሠረት የተቋቋመና በነጻ ኮሚሽን የሚመራ መሆኑም ለምክክር ጉባኤው ሂደት ተቋማዊና ሕጋዊ መሠረት መስጠቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከታች ጀምሮ የመጣበት አቀራረብም ልዩነቶችን ለማስተዳደር፣ መግባባትን ለመገንባትና ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ ለማስገኘት ጠቃሚ ተሞክሮ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አካታችና አሳታፊነት አቀራረብ ሀገራዊ መግባባትን መገንባት ለሚሹ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ተመራጭ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።