ቀጥታ፡

ወጣቱ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በመያዝ እድገትን ማፋጠን አለበት

ጎንደር፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ)፡-ወጣቱ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታና ልማት ወሳኝ ኃይል ከመሆን ባለፈ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በመያዝ እድገትን ማፋጠን እንዳለበት የሰላም ሚኒስቴር ገለፀ።

በጎንደር ከተማ ዓለም ዓቀፍ የወጣቶች ቀን "ብዝሀ የወጣቶች እውቀት ለጋራ ትልም" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሄዷል።

በሰላም ሚኒስቴር የብቃትና የሰው ሀብት አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኮሪ አብደላ በመድረኩ እንዳሉት፤ ወጣቱ ለሰላም ግንባታና ሀገራዊ ልማት ወሳኝና አሻጋሪ ኃይል መሆን አለበት።


 

ከዚህም ባለፈ በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በእውቀትና በክህሎት የታገዘ ምክንያታዊ አስተሳሰብን በማዳበር ሀገራዊ እድገትን በማፋጠን ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሰላም ሚኒስቴር ወጣቱን በማሳተፍ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም በጋራ መተባበር እንዳለበት አሳስበዋል።

የጎንደር ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉቀን ጌታሁን በበኩላቸው የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። 


 

በከተማው በሚካሔዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ወጣቶች በተለያዩ የልማት መስኮች በንቃት እየተሳተፉ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም ወጣቱ ሀገራዊ ግዴታውንና ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በግብርና፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው ያለው ደግሞ የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት አንተነህ ገብረሚካኤል ነው። 

ወጣቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለሰላምና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ማዋል እንዳለባቸው ገልጾ፣ መንግስት ባመቻቸው የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና በመሳተፍ ያገኙትን የቴክኖሎጂ እውቀት ለገቢ ምንጭ እንዲያውሉ መክሯል።

በመድረኩ ከሰላም ሚኒስቴር ተወካዮች በተጨማሪ የከተማው አመራሮችና ወጣቶችም ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም