በድሬደዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው
ድሬደዋ፣ ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተናገሩ።
በድሬዳዋ "ከሥራ ጠባቂነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት" በሚል መሪ ሐሳብ የወጣቶችን ሥነ-ልቦናዊ የሥራ ላይ ብቃት የሚያጠናክር ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በወቅቱም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንደተናገሩት፤ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው።
በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የሚገኙ ወጣቶችን በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኘው "ብቃት የሥራ ላይ የወጣቶች ሥልጠና" ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአራተኛው ዙር የተመለመሉ ወጣቶች የተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመለወጥ በቁርጠኝነት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ዙሮች የሥራ ላይ የሥልጠና መርሃ-ግብር ከ2 ሺህ 900 በላይ ወጣቶችን የሥራ ባለቤት ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የሥራ ላይ ክህሎትና ዕውቀት እንዲቀስሙ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር ብለዋል።
የዛሬ ተመልማዮችም ከተቋምና እና ኢንዱስትሪዎች ጋር በመተሳሰር የ6 ወራት የሥራ ላይ ብቃታቸውን በማረጋገጥ የሥራ ባለቤት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
ዘንድሮም ለአራተኛ ዙር ሥልጠና የተመለመሉ 1 ሺህ 800 ወጣቶች በአስተዳደሩ ሁለት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መሠረታዊ ክህሎት መር ሥልጠና ተሰጥቷቸው ለሥራ ላይ ልምምድ ዝግጁ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በቢሮው የሥራ ዕድል ፈጠራና የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አሊ፤ የድሬዳዋ አስተዳደር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ያሳየውን ቁርጠኝነት የፌደራል መንግሥት በማረጋገጡ በየዓመቱ ተጠቃሚ ሲደረጉ የነበሩ ወጣቶችን ቁጥር ከ970 ወደ 1 ሺህ 800 ከፍ እንዲል ማድረጉን አስረድተዋል።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ወጣት በአምላክ አምሳሉ እና ወጣት አፈንዲ ሙሳ፤ የተፈጠረላቸውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።