ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ ተግባር ለተተኪው ትውልድ የሚሻገር አሻራ የሚያስቀምጥ ተግባር ነው

ሰመራ፣ ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ) ፡-የበጎ ፈቃድ ተግባር የማህበረሰቡን የመደጋገፍ እሴት ከማጎልበት ባለፈ፣ ለተተኪው ትውልድ የሚሻገር አሻራ የሚያስቀምጥ ተግባር  መሆኑን የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ገለጹ።

ቢሮው በዛሬው ዕለት ድጋፍ ለሚሹ ከ500 በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችንና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እገዛ አድርጓል።


 

በድጋፍ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ እንደገለጹት፤ የተደረገው እገዛ ሀገራዊ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ነው።

እገዛው በክልሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር የመጣውን የመረዳዳት ባህል ከማጠናከሩ ባሻገር፣ ነገ ሀገር በሚረከበው ትውልድ ላይ ዘላቂ አሻራ የሚያስቀምጥ መሆኑን አብራርተዋል።


 

ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎችን በመለየት ከ500 በላይ ለሚሆኑት የትምህርት ቁሳቁስ መሰጠቱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ለዚህ ተግባር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።"

የተደረገው ድጋፍ ቦርሳ፣ ደብተር እና እስክርቢቶ የሚያካትት ሲሆን፣ ለሴት ተማሪዎች ደግሞ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጭምር ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የሆስፒታል ዲያግኖስቲክ ዴስክ ከፍተኛ ባለሙያ ሲስተር ጥሩወርቅ አክሌ በበኩላቸው፤ የክልሉ ጤና ቢሮ ያደረገው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተደረጉት ተግባራት መካከል ይህ እገዛ ተማሪዎችን ለትምህርት የሚያነቃቃና ወላጆችን ደግሞ ከወጪ የሚያድን መሆኑን አብራርተዋል።

ቢሮው ያደረገው ድጋፍ የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ በሰዎች መካከል በሚደረግ እገዛና ማጋራት መልካም ተሞክሮ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪዎቹ ዘሐራ አደን እና ፋጡማ ዓሊሚራህ በበኩላቸው፤ በተደረገላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም