አረንጓዴ ዐሻራ፦ የምግብ ሉዓላዊነት ምሰሶ - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ፦ የምግብ ሉዓላዊነት ምሰሶ
(በሙሴ መለሰ)
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአፈር መሸርሸር እና የተፈጥሮ ሀብቶች መመናመን በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ዋነኛ የህልውና ስጋቶች ሆነዋል። ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ተጠቂ ናት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ ተግዳሮቶቹን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፣ የደን ሽፋንን መጨመር፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት በወቅቱ አረንጓዴ ዐሻራ ሲጀመር የነበሩ አበይት አላማዎች ናቸው።
የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሀሳብ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ መጀመሩ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘንድሮው ዓመት ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ መቀመጡን እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የምታስተናግደው 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ድረስ የሀገሪቱን ግብ ወደ 65 ቢሊዮን ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
ሐምሌ 27/ 2018 በተካሔደው የዘንድሮው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይም 800 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ፣ 805 ነጥብ3 ሚሊዮን በመትከል ከእቅዱ በላይ ማሳካት ተችሏል።
ከ26 ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው የተሳተፉበት ይሄ መርሃ-ግብር በአጠቃላይ 294 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነበር።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ለመትከል ከታቀደው ስምንት ቢሊዮን ችግኞች መካከልም ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ መተከሉን መረጃዎች ያሳያሉ።
የአረንጓዴ ዐሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ስራ ባሻገር ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
መርሃ-ግብሩ ከተራቆቱ መሬቶች መልሶ ማገገም ባለፈ፣ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ባለው ጥረት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከተለመደው የደን ልማት በተለየ መልኩ የግብርና ደንን (Agro-forestry) በማስፋፋት የአርሶ አደሩንና የከተማውን ማህበረሰብ የምግብ ፍላጎት በቀጥታ መመለስ ላይም ያተኮረ ነው።
እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ብርቱካን፣ ቡና እና ሙዝ ያሉ የምግብና የፍራፍሬ ችግኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተተክለዋል። ይህ አካሄድ አርሶ አደሮች ከሰብል ምርት በተጨማሪ ከተተከሉት ዛፎች የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ከዛም ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የሚገኘው ተጨማሪ ገቢም የአርሶ አደሩን አቅም አሳድጎታል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮ አካባቢ ምህዳርን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
የተተከሉት ችግኞችም ትርጉም ያላቸው የዜጎችን ተጠቃሚነትና የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። ከነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆነው የጥምር እርሻ ደን ሲሆን 35 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የደን ዛፍ ነው። ቀሪው ደግሞ የከተማ ውበት ዛፎች ናቸው።
የተተከሉ ዛፎች አፈርን ከውሃ መሸርሸር በመጠበቅና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማድረግ የሰብል ምርታማነትን ያሳድጋሉ፤ እንዲሁም የደረቁ ምንጮችን በማነቃቃት የመስኖ ልማትን ያበረታታሉ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተከላው ሂደት፣ የንብ እርባታንና የእንስሳት መኖ አቅርቦትን በማሳደግ የዘላቂ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በሌላ በኩል፣ ይህ አገራዊ ንቅናቄ በከተማ ግብርና ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በከተሞች ዙሪያ የሚለሙ የፍራፍሬ ችግኞች በአነስተኛ ይዞታዎች ላይ የተመጣጠነ ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው።
ይህ አካሄድ በከተሞች የሚታየውን የምግብ ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን በመቅረፍ፣ በምግብ ራስን ከመቻል አንጻር የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያደርግ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት እና በምግብ ራስን የመቻል አገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚተገበር ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።
ንቅናቄው ከተራቆቱ መሬቶች መልሶ ማገገም ባለፈ፣ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥንበትን ሁለንተናዊ አቅም ፈጥሯል።
ኢትዮጵያዊያን እንደ አድዋ እና እንደ ህዳሴ ግድብ ሁሉ በአንድ ድምጽ በመደመር እሳቤ በአንድነት ተነስተው በጋራ እየፈጸሙት ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከችግኝ መትከልም በላይ ነው። ይሄ አንድነት ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የተላቀቀች ለቀጣናው ለአህጉሩና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአርዓያነት እያስጠቀሳት የሚገኝ ነው።
ትውልዱ በየዓመቱ በሚከናወነው በዚህ መርሃ-ግብር ዐሻራውን ከማሳረፍ ባለፈ በእንክብካቤውም የተናበበ ሆኖ መቀጠል የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን የማድረግ መሻቱን ማሳካት ይጠበቅበታል።