በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ በተከናወኑት ተግባራት ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ በተከናወኑት ተግባራት ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ነው
አዳማ ፤ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ) ፡-በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ በተከናወኑት አበረታች ተግባራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት በየደረጃው ያሉ የዞንና የከተማ አስተዳደሮች ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሴክተር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ባጫ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የሴቶችን ተሳትፎ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ተስፋ ሰጪ ስራዎች አከናውነዋል።
በዘንድሮው ዓመት 'የእናቶችን ቤት እንገንባ' በሚል መሪ ሐሳብ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ባለድርሻ አካላትንና በየደረጃው የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶችን በማስተባበር የ156 ሺህ ቤቶች ግንባታና ጥገና ተጠናቆ ርክክብ መፈጸሙን ለአብነት አንስተዋል።
ቤቶቹ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች የተሻለና ዘላቂ መኖሪያ እንዲያገኙ ያስቻሉ ከመሆኑም በላይ፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመቅረፍ ጎን ለጎን ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማጠናከርና ለማብቃት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ሴቶችን በማህበር በማደራጀት በዶሮ፣ በወተት ላምና በበግና ፍየል እርባታ እንዲሁም በእንስሳት ማድለብና በሌሎችም ሥራዎች እንዲሰማሩ መደረጉንም አመልክተዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ገጠራማ አከባቢዎች የሚኖሩ ሴቶች በማህበር ተደራጅተው የእህል ወፍጮ ኢንዱስትሪ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
በተመሳሳይ የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነትና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት በተደረገው ጥረት፣ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በመራጭነትና በተመራጭነት የተሻለ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ወይዘሮ መብራት ገልጸዋል።
አክለውም መድረኩ በአዲሱ የሴቶች ተጠቃሚነት ፖሊሲ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ሁለንተናዊ ተሳትፎአቸውንና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበት በተቀናጀ መልኩ ለመረባረብ የሚያስችል የጋራ አረዳድ ለመያዝ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
የጂማ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ አወል በበኩላቸው፣ በዘንድሮው ዓመት የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ገልጸዋል።
ለአብነትም ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች የብድር አገልግሎት ተመቻችቶላቸው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል።
ሴቶቹ በዋናነት በሩዝ፣ በአቮካዶ፣ በሙዝና ቅመማ ቅመም ልማት፤ እንዲሁም በማር፣ በዶሮና በወተት ላሞች እርባታ ዘርፍ በመሳተፍ ውጤታማና ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የሴቶችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ከአምስት ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
ከ300 በላይ የእንጀራ ምጣዶች፣ የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖችና የእህል ወፍጮዎች ድጋፍ በማድረግ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች በአማራጭ የገቢ ምንጮች ተሰማርተው ራሳቸውን በዘላቂነት እንዲችሉ መደረጉንም ተናግረዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ሞሲሳ በዞኑ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ከጥገኝነት ለማላቀቅ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ለአቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሴቶች የሚሆኑ ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉን በመጠቆም፣ በተለይም በግብርና፣ በአነስተኛ ንግድና የአገልግሎት ዘርፎች እንዲሳተፉ የተለያዩ ድጋፎችና እገዛዎችን በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።