ቀጥታ፡

የግብፅ ሚዲያዎች ስለ ህዳሴ ግድብ ከራሳቸው ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር የሚቃረን ዘገባ እያቀረቡ ነው-ጋዜጠኛና ፀሐፊ ዛሂድ ዚዳን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ):- የግብፅ ሚዲያዎች ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ወጥነት የሌላቸው እና ከበርካታ የግብፅ ሳይንቲስቶችና የውሃ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ግምገማዎች ጋር የሚጋጩ መሆናቸውን ጋዜጠኛና ፀሐፊ ዛሂድ ዚዳን ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ዛሂድ፤ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮች በሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ትንተናዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ አሻሚና እርስ በእርስ በሚቃረኑ የመገናኛ ብዙሃን ተረኮች የሚመሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

የግብፅ የጂኦሎጂ ባለሙያ ዶክተር አባስ ሸራቂ ግድቡ በተፈጥሮው በግብፅ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስ በግልጽ ካስረዱት የሀገሪቱ ባለሙያዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ጋዜጠኛው ጠቅሰዋል።

ሌላኛው የግብፅ ሳይንቲስት ዶክተር ሳመህ አርማኒዮስ፤ ህዳሴ ግድብ በወንዙ ፍሰት ላይ ምንም ዓይነት የውሃ እጥረት ሳይፈጥር ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ውሃው በቀጥታ ወደ ወንዙ የሚመለስበት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት መሆኑን ማብራራታቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የህዋ ሳይንቲስቱ ዶክተር ፋሩክ ኤል-ባዝ ግድቡ የተሻለ የውሃ አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የሱዳንን እና የግብፅንም ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ማመልከታቸውን ዛሂድ አብራርተዋል።


 

ጋዜጠኛው እንደ ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ እና የቀድሞ የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትር ኡስማን አል-ቶም ያሉ የሱዳን ባለሙያዎችን በመጥቀስ፤ ስለ አባይ ወንዝ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ በፖለቲካዊ ጩኸት ሳይሆን በሳይንሳዊና በተረጋገጡ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ ትንተና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ግድቡን በአንድ ወቅት ከጎርፍና የመሠረተ ልማት ውድመት ጋር በማያያዝ፣በሌላ ጊዜ ደግሞ የውሃ መጠን መቀነስና ድርቅ ያስከትላል በማለት የሚከሱበት መንገድ ፍጹም የሚቃረን ሀሳብ ነው ብለዋል።

ዛሂድ አክለው እንደገለጹት፤ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ አደጋ ይደቅናል የሚሉ የፖለቲከኞችና የመገናኛ ብዙሃን ውንጀላዎች ፖለቲካዊ ፍላጎትን ያዘሉ እንጂ ወጥ የሆነ ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው።

ይህ አይነቱ የተሳሳተ ትርክት ኢትዮጵያ ወደ ተፋሰሱ ሀገራት ከሚፈሰው የናይል ውሃ 86 በመቶ ድርሻ ካለው ከአባይ ወንዝ የተፈጥሮ ሀብቷ የመልማት መብቷን ለማደናቀፍ ለበርካታ አስርታት ሲከናወን የቆየ አካሄድ እንደሆነም ነው ያስረዱት።


 

አጠቃላይ የአባይ ወንዝ ዓመታዊ የውሃ መጠን በክረምቱ ወራት ወዲያው ሊታወቅ የሚችል ባለመሆኑ፣ ስለ ውሃው መጠን ቀድሞ ድምዳሜ መስጠት አይቻልም ነው ያሉት ዛሂድ።

ይልቁንም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካዊ ጩኸት በመውጣት በሳይንሳዊ ጥናቶችና በተረጋገጡ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ ዘገባ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም