ቀጥታ፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ስርዓትን በማስተማር ሀገር በቀል እውቀትን ለትውልድ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8/2018(ኢዜአ):- ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ስርዓትን ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በማስተማር ሀገር በቀል እውቀትን ለትውልድ በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በሀገር በቀል እውቀቶች፣ በማዕድን፣ በግብርናና እንስሳት ሀብት እንዲሁም በጤና ዘርፎች ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ 

ከእነዚህ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ሀገር በቀል እውቀትን የተመለከተው ሥራ በተለይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኘው የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት አማካኝነት ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ነው፡፡

ገዳ በኦሮሞ ብሔር ዘንድ ለዘመናት ሲተገበር የቆየ፣ በስምንት ዓመት ስልጣን ሽግግር የሚመራ፣ አመራርን፣ ፍትህን፣ ሰላምንና ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያካትት ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁሉን አቀፍ ስርዓት ነው። 

ገዳ ከባህላዊ ስርዓትነት አልፎ ለዘመናዊ ሀገረ-መንግስት ግንባታ፣ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መርሆዎች መጎልበትና ለሀገራዊ ማንነት ዕድገት የጎላ ሚና እየተጫወተ ያለ የኢትዮጵያ ሀብት ነው።

የገዳ ስርዓት ለሀገር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ መካከልም የግጭት አፈታት እና ሰላም፣ የትምህርትና ምርምር አስተዋጽኦ፣ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ አንድነትና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሀገር በቀል እውቀት ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው የገዳ ሥርዓትን በሚገባ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡   

ይህ ኢንስቲትዩት የገዳ ሥርዓትን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) እያስተማረ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፣ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ 

እነዚህ ምርምሮች ለዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው፣ በተለይም ከሕትመትና ዩኒቨርሲቲውን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ከማስተዋወቅ አንጻር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡


 

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር መምህርት አመርቲ አስፋው በበኩላቸው፤ የገዳ ኢንስቲትዩትን በ2011 ዓ.ም መቀረጹን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ገዳ እና የኦሮሞ ታሪክ፣ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ገዳ እና ሰላም፣ በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ደግሞ ገዳ እና አስተዳደር በሚል መርሃ ግብር እያስተማረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በቅርቡም በዶክትሬት ደረጃ የሚመረቁ ተማሪዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ስርዓተ ትምህርቱ ሲቀረጽ ቱባ የሆነው ባህል ተደራሽነት እንዲያገኝና ሰዎች እንዲማሩበት ማድረግ የሚያስገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በኢንስቲትዩቱ የገዳ እና የኦሮሞ ታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር አያና ዋሬ ገኖ በሰጡት ማብራሪያ፣ ገዳ ባህልን፣ ታሪክን፣ ባህላዊ ሥርዓትን፣ ኢኮኖሚን እንዲሁም የአኗኗር ዘዴን ጨምሮ ሰፊ ይዘት ያለው ነው ብለዋል።

ገዳ በኦሮሞ ብሔር የተቀረጸ ቢሆንም የመላው ኢትዮጵያ ቅርስ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት ማንነት አንዱ አካል ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የገዳ እና አስተዳደር የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ መንዶ ዶዮ በሰጡት አስተያየት፣ የገዳ ትምህርት የሀገር ውስጥ እውቀት እንደመሆኑ መጠን በአፍሪካ ደረጃ ብርቅ የሆነ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ከዚህ ቀደም አብዛኛው ሥርዓት፣ አስተዳደርም ሆነ ባህል ከውጭ ሀገራት ሲቀዱ የቆዩ መሆኑን አስታውሰው፤ የገዳ ሥርዓት ግን የራሱን ብሔረሰብ ውስጣዊ እሴት ወስዶ በማሳደግ ወደ ስርዓተ ትምህርት በማምጣትና በፒኤችዲ ደረጃ በማስተማር ለአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ገዳ በትምህርት መልክ መሰጠቱ በአፍ ብቻ ይተላለፍ የነበረውን እውቀት በጽሁፍ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ብሎም ስርዓቱን ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ሀገር በቀል እውቀትን በዘመናዊ የትምህርት ስርዓት በማካተት፣ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ በማስተማርና ምርምር በማካሄድ የገዳ ስርዓትን ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ተደራሽ ለማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ገዳ ስርዓት ኢትዮጵያ ካላት የተለያዩ ባህላዊ ሀብቶች መካከል አንዱ ሲሆን በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ በመመዝገብ ለሀገሪቱ ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፏል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም