ቀጥታ፡

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ኢትዮጵያን ከገናና የዕድገት እና ሥልጣኔ ታሪኳ ጋር የማስታረቅ የሕልውና ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ኢትዮጵያን ከገናና የዕድገትና ሥልጣኔ ታሪኳ ጋር የማስታረቅ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ቀንድ እና የውኃ ጂኦፖለቲካ ከፍተኛ ተመራማሪ ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር) ገለጹ።

ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከገናና ሥልጣኔዋ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች አስታውሰዋል።

በአክሱም ሥልጣኔ ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊትና በኋላ በነበሩት ዘመናት፣ ኢትዮጵያ የንግድና የውጭ ግንኙነቷን በቀይ ባሕር ቀጣና በባሕር በርና የወደብ አገልግሎቶች አማካኝነት ታሳልጥ እንደነበር ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማሳጣት የውስጥ እና የውጭ ባዕዳን ኃይሎች በየዘመናቱ ያልሸረቡት ሴራና ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበርም አስረድተዋል።

ታሪካዊ ጠላቶች የሚሸርቡትን ሴራ በመመከትና በማክሸፍ፣ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነቷን ለሺህ ዘመናት አስጠብቃ መቆየቷን አብራርተዋል።

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድንና የሻዕቢያ ስብስብ ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃም ሆነ አመክንዮ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ከገናና ታሪክና ሥልጣኔዋ ጋር በእጁጉ ከተቆራኘው ቀይ ባሕር እንድትገለል መድረጉን አመልክተው፤ በሀገሪቷ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል መፈጸሙን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ላይ የተፈጸመው ክህደትም በሀገሪቷ ዕድገትና ብልፅግና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ባሕር በር አልባነት ከሀገሪቷ የንግድና የሎጂስቲክስ አቅም ጋር ተያይዞ በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ከፍተኛ የወደብ ኪራይና ሌሎች የገንዘብ ወጪዎችን እንድታወጣም እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ መልኩም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚንቀሳቀሱ የሽብር ኃይሎች የሚፈጥሩትን የሰላምና ደኅንነት ስጋት ለመመከት ከባሕር በር ባለቤትነት መገለሏ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የትውልድን መጻኢ ዕጣ ፈንታ የሚወስን የብሔራዊ ጥቅምና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው የታሪክ ስብራትን የማረምና ኢትዮጵያን ከገናና ታሪክና ሥልጣኔዋ ጋር የማስታረቅ ጉዳይም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር የአፍሪካን ኢኮኖሚ ውህደት ለማሳለጥ በምታደርገው ጥረት የባሕር በር ባለቤትነትን ጥያቄውን ምላሽ ማስገኘት እንደሚያስፈልግ አስረጂ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት፣ የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው ዓለም አቀፍ ቅቡልነት እያገኘ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ለዚህም ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኅን የጉዳዩን አስፈላጊነት በቅጡ መገንዘባቸውን አብራርተዋል።

በቀጣይም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ መክረዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያውያን በሁሉም መስክ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄውን በበለጠ በማስገንዘብ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም