የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦የእናቶችና የሕፃናት ጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የልህቀት ማዕከል ያቋቋመው የፅንስ ምርመራና ሕክምና ማዕከል (Fetal Diagnostic and Intervention Center) ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃው መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ እንደገለጹት፤ የጤናውን ዘርፍ በማዘመንና በማሳደግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።
የጤና ተቋማትን መሰረተ ልማቶች የማሻሻል፣ በሽታን የመከላከልና የጤና ፖሊሲውን ከመከላከል ወደ መከላከል እና አክሞ ማዳን በመለወጡ በርካታ ለውጦች ተገኝተዋል ብለዋል።
የሕጻናትና የእናቶች ጤና አገልግሎት ሽፋንና ጥራትን ለማጎልበት እና የባለሙያዎችን አቅም የማሳደግ ስራዎች በልዩ ትኩረት እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት የተመረቀው የፅንስ ምርመራና ሕክምና ማዕከል የእናቶችን ጤና በመጠበቅ ሕጻናት ከመወለዳቸው በፊት በማህጸን ውሰጥ እያሉ በቂ ክትትልና ህክምና በማድረግ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም አንድ ህጻን ከመወለዱ በፊት በቂ ክትትልና ተገቢው የህክምና ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም የጤና ቱሪዝምን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ገልጸዋል።
ማዕከሉ በዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና የህክምና ባለሙያዎች የተደራጀ መሆኑን አብራርተው፤ የህክምና አገልግሎቱ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች እንዲስፋፋ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።