ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራችን ጉዳይ እኩል የመሳተፍና የመወሰን ዕድልን አረጋግጦልናል

ጂንካ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ እኔ አውቅልሃለው የሚለውን አግላይ አካሄድ በማስቀረት ዜጎች በሀገር ጉዳይ እኩል የመሳተፍና የመወሰን መብታቸውን ያረጋገጠ መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የበና ፀማይ ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮችን መፍትሄ በመስጠት ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ልማትን በማስፈን ለሁሉም የምትመች ሀገር ለመገንባት ጉልህ ሚና እንዳለው የታመነበት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ ኢዜአ በበናፀማይ ወረዳ ያነጋገራቸው አርብቶ አደሮች እንዳሉት፤ ምክክሩ ለሁሉም ዜጎች በሀገር ጉዳይ ላይ እኩል የመሳተፍና የመወሰን እድልን ከመስጠት ባለፈ የቆዩ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ያስችላል።

ከአርብቶ አደሮቹ መካከል የበናፀማይ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ አቶ  ጀሞ ቦሎቾ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ ቀደም የመደመጥ ዕድል ላላገኘው የአካባቢው አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  ጭምር የመደመጥና በሀገሩ ጉዳይ ከሌሎች እኩል ውሳኔ የመስጠት መብቱን እንዳረጋገጠለት ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የአርብቶ አደሩ አካባቢ የግጭት ቀጠና እና የሰላም እጦት በስፋት የሚስተዋልበት እንደነበረ አስታውሰው፥ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የተለዩ አጀንዳዎች መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቁጭ ብለው መምከራቸው ለቆዩ ችግሮችና አለመግባባቶች መፍትሄ ለማምጣት ያስችላቸዋል ያሉት የሀገር ሽማግሌው፣ የምክክሩ ውጤትም ለአካባቢያቸውም ተጨባጭ ውጤት ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። 

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርብቶ አደር ጋርሾ ማያ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ተሳታፊዎች አካታች በሆነ መንገድ የተመረጡ እና የእነሱም ወኪሎች የተገኙበት መሆኑንን ገልጸዋል። 


 

ይህም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በምክክሩ እንዲደመጡና በሀገር ጉዳይ የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

እንደ አርብቶ አደር ጋርሾ ገለጻ፣ የምክክር ሂደቱ ሁሉንም ማህበረሰብ በየደረጃው ያሳተፈ እና የሁሉም ሀሳብ የተካተተበት ስለሆነ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና እድገት መረጋገት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ 

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን ተለይተው ውይይት እየተደረገባቸው ያሉ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችም በየአካባቢው የሚነሱ ፍላጎቶችን ያማከሉ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በአጀንዳዎች ላይ የሚደረስበት መግባባትም ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገር ለመገንባት ያስችላል ብለዋል። 

ምክክሩ ሀገርን ተብትበው ከያዙ ችግሮች በማላቀቅ ወደከፍታ ማማ የሚያወጣት ታሪካዊ ዕድል ነው ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አርብቶ አደር አርቲ ማያ ናቸው።


 

የግጭትና ያለመግባባት መንስኤዎች ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድልን ማጣት መሆኑን ጠቁመው፣ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን የመመካከር ባህልን በማሳደግ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገር መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል። 

የምክክር ጉባኤው ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመድረሱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ምክክሩ ሁሉን በእኩል አሳታፊ መሆኑ እኔ አውቅልሃለው የሚለውን አግላይ አካሄድ አስቀርቷል ብለዋል።

 ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው ዋናው የምክክር ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በተለዩ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም