በአማራ ክልል ከ337 ሺህ ሄክታር በላይ የኮትቻ አፈርን በማንጣፈፍ ሰብል ማልማት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ337 ሺህ ሄክታር በላይ የኮትቻ አፈርን በማንጣፈፍ ሰብል ማልማት ተችሏል
ባህርዳር ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከ337 ሺህ ሄክታር በላይ የኮትቻ አፈርን በማንጣፈፍ ሰብል ለማልማት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች በስፋት የሚገኘውና ከፍተኛ ለምነት ያለው የኮትቻ አፈር፣ ተገቢው የአፈርና ውሃ እንክብካቤ ከተደረገለት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የማፋጠን አቅም እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ይገለፃሉ፡፡
አርሶ አደሮች ዘመናዊ የውሃ ፍሳሽና የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ አዳዲስ አሰራሮች በመተግበር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
የቢሮው የአፈር ለምነት ባለሙያ አቶ አምሳሉ አድማስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኮትቻ አፈር የተሸፈነን መሬት በዘመናዊና በባህላዊ መንገድ በማንጣፈፍ በሰብል የማልማት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻ 689 ሺህ 533 ሄክታር የኮትቻ አፈርን በማንጣፈፍ ለማልማት ታቅዶ በተከናወኑ ተግባራት እስካሁን ከ337 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
በዚሁ የኮትቻ አፈር ልማት ላይ ከ468 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን፤ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ ባቄላ እና ሌሎችንም ሰብሎች እያለሙ ይገኛሉ።
እስከያዝነው ወር ማብቂያ ድረስም በዕቅድ የተያዘውን መሬት አጠንፍፎ በጤፍና በሌሎች ዘግይተው በሚዘሩ ሰብሎች በማልማት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ጌታሁን መንግሥት በበኩላቸው፤ ግማሽ ሄክታር የሚሆነውን የኮትቻ ጥቁር አፈር መሬታቸውን በማንጣፈፍ የስንዴ ሰብል እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለዓመታት ውሃ ተኝቶበት ይከርም የነበረውን መሬት ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያን ተጠቅመው በማንጣፈፍ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ እስከ 18 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ አርሶ አደር ልንገር ወርቁ፤ ቀደም ሲል ውሃ ይተኛበት የነበረውን የኮትቻ አፈር መሬታቸውን በማንጣፈፍ ስንዴ፣ ጤፍና ቦሎቄ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የመኸር እርሻም መሬታቸውን በማንጣፈፍ በስንዴና በጤፍ ያለሙ ሲሆን፣ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የቢሮው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በክልሉ በ2017/2018 የምርት ዘመን በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያና በባህላዊ ዘዴ ውሃን በማንጣፈፍ ከለማው 600 ሺህ ሄክታር ገደማ መሬት አበረታች ምርት ተገኝቷል።