ቀጥታ፡

የመዲናዋ አስደናቂ ልማት መንግስት የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የሚከናወኑ አስደናቂ የልማት ስራዎች መንግስት የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት መርቀው በይፋ ለህዝብ ክፍት ባደረጉበት ወቅት፣ ፕሮጀክቱ የግንባታ ስኬት ብቻ ሳይሆን መዲናችንን የአየር ንብረት ለውጥ የምትቋቋም ያደርጋል ብለዋል።


 

በተጨማሪም አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ስልታዊ ሽግግር እንደሚያፋጥንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀበና ወንዝ የቀድሞ ገጽታ በመቀየሩ ምክንያት ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን እና በምሽትም የሚዝናኑበት፣ የሚያሰላስሉበት እና ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚከውኑበት ማራኪ ስፍራ ሆኗል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው ጎብኚዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ይህ አስደናቂ የልማት ስራ መንግስት የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር የሚያደርገውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የቱሪስት አስጎብኚዋ ምሕረት አሰፋ እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት የልማት ስራዎች እጅግ አስደናቂ ናቸው።

በሌሎች አገራት በጉብኝት ወቅት የተመለከተቻቸውን የከተማ ልማት ስራዎች በኢትዮጵያም ማየቷ እንዳስደሰታት ተናግረዋል።

እነዚህ የመዝናኛ ስፍራዎች ከቱሪዝም ባሻገር ለህብረተሰቡ ንጹህ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አንስተዋል።

ህጻናት እና ታዳጊዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጫወቱባቸውና ነዋሪዎችም ለጤናቸውና ለዕረፍት የሚጠቀሙባቸው ስፍራዎች መፈጠራቸው መንግስት ለዜጎች የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

የቀድሞው የቀበና ወንዝ አካባቢ በቆሻሻ የተሞላ እንደነበር የሚያስታውሰው ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ መለሰ ከበደ፣ አሁን ላይ ግን አካባቢው ውብ እና ለኑሮ ተስማሚ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።


 

ይህ የልማት ስራ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ፣ ለቱሪዝም እና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑም አንስተዋል።

በአካባቢው እንደመኖራቸው  መጠን ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን በቀበና ወንዝ አካባቢ የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ አዝናኝ እና አስደሳች መሆኑንም ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ አዳዲስ የመዝናኛ ስፍራዎች ጤናማ ትውልድ እና አካባቢን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

እሸቱ አማረ በበኩላቸው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአዲስ አበባ እንዲህ ያሉ ዘመናዊ የመዝናኛ ሥፍራዎች እጥረት በመኖሩ ነዋሪዎች ከከተማ ውጭ ወደ ሆኑ አካባቢዎች ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ግን በአዲስ አበባ እንዲህ ያለ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።


 

በተለይም ህጻናት አእምሯቸውን የሚያድሱበትና ንጹህ አየር የሚያገኙበት በመሆኑ ለዕድገታቸውም ሆነ ለጤናቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም አዲስ አበባን የጎበኙት ከድሬዳዋ የመጡት ሁስኒያ አብዲ፣ የከተማዋ ገጽታ በኮሪደር ልማት ስራዎች ተቀይሮ መመልከታቸው እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።

በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት እና የጽዳት አጠባበቅ ከተማዋን እጅግ ውብ እና ሳቢ እንዳደረጓትም ገልጸዋል።

ከባሌ ሮቤ የመጡት ሁሴን አህመድ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረው እና አሁን ባለው የከተማዋ ዕድገት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በስራ ምክንያት አድካሚ ቀናትን የሚያሳልፉ የተለያዩ ሰራተኞች፣ ከስራ ውጪ አእምሯቸውን ዘና የሚያደርጉበትና የሚያሳርፉበት ቦታ ማግኘታቸው እጅግ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ለመዲናችን ውበትን ከማጎናጸፍ ባለፈ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም