ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅሟን በማሳደግ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅሟን በማሳደግ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማመንጨት አቅሟን በማሳደግ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስና የጂኦተርማል ብዝኅ የኃይል ፀጋዎች ልማት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ማጎልበት የሚቻልበት ምኅዳር እየፈጠረ ይገኛል።
የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞም የኤሌክትሪክ ማመንጨትን ከልማት፣ ልማትን ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ኢኮኖሚ ዕድገትን ከቀጣናዊ ትስስር ጋር እያሰናሰለ የሚገኝ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብ ነው።
ሚኒስትር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ዘላቂ ኢኮኖሚ እንድትገነባ እያስቻለ ነው።
የታዳሽ ኃይል ምንጮቹን በማቀናጀት የሚካሄደው ልማትም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የከተማ ልማትና የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የኃይል መሠረተ ልማት እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስና የጂኦተርማል ሃብቶችን በማልማት የኤሌትክትሪክ የኃይል ምንጮችን፣ ደህንነትና ዘላቂነትን በማጎልበት የኢኮኖሚ መሠረት መፍጠር እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በዜጎች ትብብርና በሀገር አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አስረድተዋል።
የሕዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦት አቅም የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት ከማገዙ ባሻገር፣ ኃይልን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር አዲስ ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
ይህም ኃይል ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት የሚውል ግብዓት ብቻ ሳይሆን የንግድ፣ የዲፕሎማሲና የቀጣናዊ ትብብር መሣሪያ እየሆነ መምጣቱን እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
የዓለም አቀፍ የውሃና የኃይል ገበያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታን ታሳቢ በማድረግም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በማልማት ከሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎት ባሻገር ቀጣናዊ ትስስርን እያሰፋች መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት እመርታዊ ጉዞም ኃይልን ከማመንጨት የተሻገረ ቀጣናዊ የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን የማፋጠን አህጉራዊ የልማት ግብ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በዚህም ስትራቴጂካዊ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በማልማት የራሷን የኃይል ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስርና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ውህደት የሚያግዝ አዲስ ምዕራፍ እየገነባች ነው ብለዋል።
ለአብነትም ከጅቡቲ፣ ኬንያና ሌሎች ጎረቤቶች ጋር ያለውን የኃይል ትስስር በማስፋፋት የጋራ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያጎለብቱ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብና የኃይል ትስስር መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኃይል ሽያጩም ኢትዮጵያን የኃይል ማዕከል በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጭ በመሆን ጭምር ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር ተሰናስሎ መቀጠሉን ተናግረዋል።