የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድነትና የሰብአዊነት ትልቁ መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድነትና የሰብአዊነት ትልቁ መገለጫ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2018 (ኢዜአ) ፦ የበጎ ፈቃድ ተግባር የአንድነትና የሰብአዊነት ትልቁ መገለጫ ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የክረምት በጎ ፈቃድ የተቋማት አፈፃፀምን ጨምሮ፣ የሴፍቲኔት፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተከናወኑ ተግባራትና ሌሎች ኢኒሼቲቮችን ገምግሟል።
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት የበጎ ፈቃድ ተግባር የአንድነትና የሰብአዊነት ትልቁ መገለጫ ነው።
ዛሬ ለአንድ ሰው የዘራነው ተስፋ ነገ ለማኅበረሰባችን የሚያፈራ ፍሬ ይሆናል፣ ዛሬ የረዳነው ወገን ነገ ሌላውን ለመርዳት የሚነሳ ዜጋ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በጎ ፈቃድ አንድ ጊዜ የሚደረግ ተግባር ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር የመልካምነት ባህል በመሆኑ ባህሉን በማዳበር ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የቅዳሜ ገበያዎችን ተደራሽ በማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ማጎልበት እንደሚገባ ገልፀዋል።
ዜጎችን ከተረጂነትና ከጥገኝነት በማላቀቅ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ምርታማነታቸውን በማሳደግ የተጀመሩ ተግባራትም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ሁሉም አመራር የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ የመንግስት እና የፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።