በምክክር ጉባኤው እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር ጉባኤው እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከተመካካሪዎች እየተነሱ የሚገኙ ሀሳቦች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገትና የተሻለ መጻኢ ጊዜ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
ተመካካሪ አበራ አኔቦ፤ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ሀገርን ወደፊት የሚያሻግሩና የጋራ ሀገርን መገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች ከተመካካሪዎች እየተነሱ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ምክክር ለሀገራችን ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ እና ለመጪው ትውልድም መልካም አርአያ የሚሆን ታሪካዊ ጉባኤ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ላለው ዘላቂ ዕድገት ምቹ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ታላቅ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ተመካካሪ ወይዘሮ ኦድንጊሊ ሎ፤ አካታች እና አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ወቅት መከናወኑን ሂደቱም የተሳካና የኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ የሚያስቀጥሉ መልካም አጋጣሚዎችን መፍጠሩን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያንን በተወካዮቻቸው በምልዓተ ያሳተፈ መሆኑንና ኢትዮጵያን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችሉ ጠቃሚ ሀሳቦች በነጻነት እንዲነሱ ምቹ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ የሀገሪቱን ብዝሃነት ያንጸባረቀ እና ሀገራዊ አንድነትን ያጠናከረ አዎንታዊ የምክክር ጉባኤ እንደሆነም ነው ያነሱት።
ሌላኛው ተመካካሪ ታደሰ ዳኜ በበኩላቸው፤ ለሀገር አንድነት ምክክር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝና መልካም ውጤት ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የወከሉ ተመካካሪዎች በነጻነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ እየተመካከሩ በመሆኑ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ ነው ብለዋል።