የምክክር ጉባኤው የዘመናት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች የቀረቡበት ነው-ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የዘመናት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች የቀረቡበት ነው-ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን ለመፍታትና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የጋራ የመፍትሔ ሀሳቦች የቀረቡበት መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ዋናው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በምክክሩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች፤ ምክክሩ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጋራ የመፍትሔ ሀሳብ የቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከተመካካሪዎች መካከል አቶ ነኢ አለልኝ ምክክሩ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ጠቃሚ ግብአቶች የተገኙበት ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮች ላይ በስፋት ተመካክረን የመፍትሔ ሀሳቦችን አስቀምጠናል ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ኒሽራ ሱሌይማን ሀሳባችንን በነጻነትና በግልጽ በማቅረብ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ምክክር እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
ምክክሩ መግባባት የሰፈነባት ያደገችና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
ምክክሩ ለሀገር የሚበጁ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ደራራ ጣፋ ናቸው።