ቀጥታ፡

በመሶብ የአንድ ማዕከል ያገኘነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ጊዜያችንን ለመቆጠብ አስችሎናል

ሀዋሳ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ በሃዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል ያገኘነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንግልትን በማስቀረት ጊዜያችንን ለመቆጠብ አስችሎናል ሲሉ ተገልጋዮች ገለጹ።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የመሰሉና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮች አገልግሎትን የሚያቀላጥፉና የተገልጋይ እንግልትን የሚያስቀሩ የመደመር መንግስት እሳቤ ፍሬዎች ናቸው። 

አገልግሎቱ አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በማስወገድ፣ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በመሰብሰብ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጊዜን ከቀናት ወደ ደቂቃዎች በማሳነስ የዜጎችን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ እንዲቆጠብ እያደረገ ይገኛል።

የሐዋሳው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የሚሰጠው ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ከዚህ ቀደም የነበረውን የጊዜ ብክነትና እንግልት እየቀነሰ መሆኑን ተገልጋዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ደሳለኝ ፋንታ የተባሉ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ የንግድ ፈቃድ ለማሳደስ ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ በ10 ደቂቃ ውስጥ ጉዳያቸውን መጨረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ማዕከሉን ለማስፋፋት የወሰደውን ቁርጠኝነት ያደነቁት ተገልጋዩ፤ ዜጎችም ለውጤታማነቱ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

የማዕከሉ አገልግሎት የተደራጀና ዘመኑን የዋጀ በመሆኑ ከዚህ ቀደም የሚስተዋሉ መጉላላቶች ቀርተው ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ ተገልጋይ ወይዘሮ ሰላማዊት ከፈለኝ ናቸው፡፡

ለስም ዝውውርና ለንግድ ፈቃድ እድሳት መምጣታቸውን ጠቅሰው በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፤ የተለያዩ ተቋማት በአንድ ማዕከል ውስጥ መኖራቸው አሠራሩን ቀልጣፋ አድርጎታልም ብለዋል፡፡

አቶ ሸምሱ ተስፉ የተባሉ  የማዕከሉ ተገልጋይ በበኩላቸው፤ የማዕከሉ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር በደቂቃዎች ውስጥ የመጡበትን ጉዳይ ለመፈፀም እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ይህም ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን እንደቆጠበላቸው ገልጸው፤ መንግሥት ማዕከሉን በማስፋፋት በአገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመረው ሥራ ውጤታማ መሆኑን መስክረዋል፡፡

መሶብ የተገልጋይን እርካታ ከማሳደግ ባለፈ የሠራተኛውን የሥራ ባህል የቀየረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ የሐዋሳ ከተማ መሬት አስተዳደርና ኢንቨስትመንት መምሪያ ቡድን መሪ አዛሪያስ አስማማው ናቸው፡፡


 

በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት የሚፈጸምበትን የጊዜ ገደብ በማሻሻልና ቅድሚያ ማግኘት የሚገባቸውን በመለየት ጭምር የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሐዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ የሚሰጠው ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔን ያመጣ ነው ብለዋል፡፡


 

ባሳለፍነው ግንቦት ወር መጨረሻ ሥራ በጀመረው የሐዋሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 13 የሚደርሱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት 57 አገልግሎቶችን እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በማዕከሉ እስካሁን ከ37 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸው፤ ተገልጋይ ተኮር የሆነው አሰራር የተገልጋይ እርካታን እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም