ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከለማው መሬት እስካሁን ከ21 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ እስካሁን ከ21 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል የበልግ እርሻ ልማት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭና የምግብ ዋስትና መሰረት ነው። 

በክልሉ በበልግ ዝናብ የሚከናወነው ይህ የግብርና እንቅስቃሴ አርሶ አደሩ የምግብ ፍላጎቱን እንዲሸፍን ከማስቻሉም በላይ፣ ገበያን ለማረጋጋት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። 

በተለይም እንደ ቦረና፣ ጉጂና አርሲ ባሉ አካባቢዎች በበልግ እርሻው የከብት መኖን ከማልማት ባሻገር ዋና ዋና የህብረተሰቡ የፍጆታ ሰብሎች የሚመረቱበት በመሆኑ ለክልሉ ግብርና መነቃቃት ቁልፍ ሚና ይጫወታል።


 

ክልሉ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የሜካናይዜሽን አጠቃቀምን በማስፋት፣ የአርሶ አደሩን የሙያ ብቃት በማሳደግ እና የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱ በማቅረብ ረገድ ያሳየው ቁርጠኝነት ለአፈፃፀሙ መሳካት ዋና ምክንያት ሆኗል። 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በበልግ ወቅት ወደ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለምቶ ወደ ምርት መሰብሰብ ተገብቷል።

ለበልግ እርሻው ውጤታማነት ለአርሶ አደሩ የሙያ ብቃትን የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን፣ ባለሙያዎች በመስክ በመገኘት ያልተቋረጠ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመው፤ ከዚህ በተጨማሪም ሰብሉን ከተባይና ከአረም ለመጠበቅ የሚያስችሉ የፀረ-ተባይና የፀረ-አረም መድሃኒቶች አቅርቦት መመቻቸቱን ገልጸዋል።


 

በዚህም በዘንድሮው የበልግ እርሻ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በሚሆነው ላይ የደረሱ ሰብሎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ ከዚህም 21 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

የምርት አሰባሰቡን ቀልጣፋና ከብክነት የጸዳ ለማድረግ በግብርና ሜካናይዜሽን አማካኝነትና  የሰው ኃይልን በማቀናጀት እየተካሄደ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

እስካሁን ከተሰበሰቡት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል፡ ጤፍ፣ስንዴ፣ገብስ፣ሰሊጥ፣ማሾ እና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል የበልግ እርሻው በስፋት የተካሄደው በ11 ዞኖች ውስጥ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ እና የምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አክለዋል።

በቀጣይም ቀሪዎቹን የሰብል ምርቶች በወቅቱና ያለ ብክነት ለመሰብሰብ የተጀመረው የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቢሮው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም