በካፋ ዞን የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የአርሶ አደሮችን ገቢ እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በካፋ ዞን የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የአርሶ አደሮችን ገቢ እያሳደገ ነው
ቦንጋ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የተሰማሩ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነታቸው እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናገሩ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በበኩሉ በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን አስታውቋል።
በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ መሻማሊ ቀበሌ በዓሣ ልማት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደር አባቢያ አባጨብሳ እንዳሉት፤ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በጓሯቸው ለአሣ እርባታ የሚሆን ኩሬ በማዘጋጀት አሣ እያመረቱ ነው፡፡
ምርቱን ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለሽያጭ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግስታዊ ካለሆነ ድርጅት በተደረገላቸው ድጋፍ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ተጨማሪ ኩሬዎችን በማዘጋጀት የዓሣ ልማት ሥራቸውን ማስፋፋታቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው ሒንጊዶ ቀበሌ በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደር ብርሃኑ ወልደሰንበት በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ዶሮዎችን ሲያረቡ ለአውሬ ይጋለጡ እና የእንቁላል ምርታቸውም ዝቅተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ግን ባገኙት ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው የዶሮ ቤት በማዘጋጀትና የተመጣጠነ መኖ ተጠቅመው በማርባታቸው የእንቁላል ምርትና ምርታማነትን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።
ያመረቱትን እንቁላል ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በንብ ማንብ ሥራ ላይ የተሰማሩት የዶማ ቀበሌ አርሶ አደር ዳንኤል ቶሌ በበኩላቸው፣ በአምስት ባህላዊ ቀፎዎች ሥራ እንደጀመሩ ገልፀው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ሥራቸውን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በመርሀግብሩ በተደረገላቸው የንብ ቀፎና ሙያዊ ድጋፍ ታግዘው በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎች እንዳሏቸው ገልፀዋል።
ከዚህም በዓመት ሁለቴ ማር እንደሚሰበስቡ ገልጸው፣ በአንድ ዙር ብቻ ከሚሰበስቡት የማር ምርት እስከ 168 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ 2ሺህ 763 የወተት፣ የዶሮ፣ የዓሣ፣ የማር እና የከብት ሥጋ መንደሮችን በማደራጀት ከ130 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ በክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታመነ በቀለ ናቸው።
መንደሮችን ከማደራጀት ባለፈ ለአርሶ አደሩ ስልጠና በመስጠት፣ በግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የተጠናከር የድጋፍና ክትትል ሥራ በመሰራቱ በሁሉም ፓኬጆች ጥሩ መሻሻሎች ታይተዋል ብለዋል፡፡
በተለይም የዝርያ ማሻሻያ ፣ የአረንጓዴና ምጥን መኖ ልማትና አቅርቦት ላይ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ መጠን ማሳደጉን አቶ ታመነ ተናግረዋል።
በዚህም የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ከመጀመሩ በፊት በክልሉ በዓመት ይመረት የነበረው የወተት ምርት ከ307 ወደ 392 ሚሊዮን ሊትር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።
የእንቁላል ምርትን ከ335 ወደ 362 ሚሊዮን፣ የማር ምርት ከነበረበት 66 ሺህ ቶን ወደ 79 ሺህ ቶን እንዲሁም የዓሣ ሥጋ ምርትን ከ4ሺህ 615 ቶን በአማካይ ወደ 7ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ምርታማነት ማደጉም የህብረተሰቡ የምግብና ስነምግብ ሥርዓት እንዲሻሻል ከማድረግ ባለፈ ተኪ ምርትና የኤክስፖርት ምርቶች በመጠንና በጥራት እንዲያድጉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
በቀጣይም በተቀናጀ መልኩ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።