የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የኩታ ገጠም አሠራርን በመጠቀማችን ምርታማነታችን ጨምሯል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የኩታ ገጠም አሠራርን በመጠቀማችን ምርታማነታችን ጨምሯል-አርሶ አደሮች
ጋምቤላ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የኩታ ገጠም አሠራርን በመጠቀማችን ምርታማነታችን ጨምሯል ሲሉ በጋምቤላ ክልል የአኙዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶ አደሮቹ፤ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የኩታ ገጠም አሠራርን በመጠቀማቸው ምርታማነታቸው ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዞኑ የአቦቦ ወረዳ ሞዴል አርሶ አደር ወይዘሮ አጁሉ ኪሩ በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ሲያለሙ ከራስ ፍጆታ ያለፈ ምርት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ማልማት በመጀመራቸው የተሻለ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮም ካለሙት ማሳ ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የእርሻ ትራክተር በመጠቀም በኩታ ገጠም እርሻ ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ማሽላና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ከራሳቸው አልፈው ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ የጠቀሱት ደግሞ የዲማ ወረዳ አርሶ አደር አቶ ወርቅነህ ይርዳው ናቸው።
በዞኑ የአቦቦ ወረዳ የመንደር 13 አርሶ አደር አቶ በለጠ አባተ፤ የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን በመከተል ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም በክላስተር ተደራጅተው በጋራ ማምረት በመቻላቸው ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
የአኝዋህ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኝኬው ጊሎ፤ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
አርሶ አደሮቹ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው እንዲያመርቱ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያ አቅርቦት መመቻቸቱን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የምርት ዘመን መጠነኛ የዝናብ መቆራረጥ መከሰቱን የጠቀሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ ይህንን ተከትሎ የምርት መቀነስ እንዳያጋጥም በአጭር ጊዜ በሚደርሱ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የመኸር ወቅት ለማልማት ከታቀደው 180 ሺህ ሄክታር መሬት አብዛኛው በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።