በደቡብ ወሎ ዞን በመኸር እርሻ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በመኸር እርሻ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል
ደሴ ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን በመኸር እርሻ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዞኑ ለስንዴ ልማት ምቹና ተስማሚ የአየር ንብረት ባለቤት በመሆኑ የስንዴ ሰብል በስፋት እየለማ ይገኛል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከለማው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 166 ሺህ 450 ሄክታሩ በኩታ ገጠም አሰራር የተሸፈነ ሲሆን፣ ከዚህም ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
የኩታ ገጠም ልማት አርሶ አደሩ በወቅቱ ግብዓትና ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኝ፣ በጋራ ለማረስ እና ለመዝራት እንዲሁም ተባይና አረምን በትብብር ለመከላከል የሚረዳ ከመሆኑ ባሻገር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ ምርት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ ማሳውን በየቀኑ በማሰስና የአረም መከላከል ስራዎችን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።
በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ015 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ እሸቱ ፤ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን በኩታ ገጠም ዘዴ ስንዴ ማልማታቸውን ገልፀዋል።
ከግብርና ባለሙያዎችም ድጋፍ እና ግብዓት በወቅቱ በማግኘታቸው ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በተንታ ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሀመድ አህመድ፤ አንድ ሄክታር መሬታቸውን በኩታ ገጠም አልምተዋል።
ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ማሳቸውን በዘር የሸፈኑ ሲሆን የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በ2018/2019 የመኸር ወቅት በአጠቃላይ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 433 ሺህ ሄክታር መሬት ከ15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።