በክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ለማልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ለማልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ
ጋምቤላ፤ነሐሴ 8 /2018(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት በማልማት የታለመውን የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የመደመር መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ፤ የትናንት የታሪክ ሀብትን፣ የዛሬውን ልማት እና የነገውን ብልጽግና በማቀናጀት ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ግብ አለው።
እሳቤው ቱሪዝምን ከቀደመው የተበታተነና የተወሰነ አካባቢ ላይ ብቻ ያተኮረ አሠራር በማውጣት፣ ከሌሎች አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች (እንደ መንገድ፣ አየር መንገድ እና ሆቴሎች) ጋር ተሳስሮ የሚተገበር ጉዳይ እንደሆነ ያሳያል።
በእነዚህ አዳዲስ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች አማካኝነት የሀገርን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባለፈ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በማላቅ ውጤት እንዲያመጣ ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
የጋምቤላን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ልማት የሚውል ሰፊ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ።
የጋምቤላ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኮንግ ሬት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት በማልማት የታለመውን የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ።
በተለይም በክልሉ እምቅ የብዝሃ ሕይወት ሀብት ያለውን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ከ"አፍሪካ ፓርክስ ኔትወርክ" ጋር በመቀናጀት ለማልማት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በፓርኩ የሚገኙት የዱር እንስሳት የክረምትና የበጋ እንቅስቃሴያቸውን መሠረት ያደረገ የመዳረሻ ቦታዎችን ለማልማት በአውሮፕላን የታገዘ የቅኝት፣ የሰርቬይና የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በባዮስፌር የተመዘገቡትን የተፈጥሮ ደኖችን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን ለማልማት የጥናትና ልየታ ሥራዎች መከናወናቸውን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
በቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ መሠረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ደርባቸው ሸዋለም በበኩላቸው፤ በክልሉ 109 የቱሪዝም መስህቦችን በጥናት በመለየት እንደየ ሀብት አቅማቸው በቅደም ተከተል ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ያለውን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ያለበትን የመሠረተ ልማት ተግዳሮት ለመፍታትና የዘርፉን ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል ከ"አፍሪካ ፓርክስ ኔትወርክ" ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በፓርኩ አቅራቢያ በሚገኘው በአሌሮ ግድብ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ሎጆች ለመገንባት የግንባታ ግብዓቶች መቅረባቸውንም ገልጸዋል።