ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቷን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማሸጋገር መሠረታዊ ለውጥ እያደረገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቷን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማሸጋገር መሠረታዊ ለውጥ እያደረገች ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቷን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለማሸጋገር መሠረታዊ ለውጥ እያደረገች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ቤተ-መጽሐፍት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከብሯል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና አሜሪካ ሁሉን አቀፍ ትብብርና አጋርነት ከምዕተ ዓመት የተሻገረ ነው፡፡
በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል በትምህርት ዘርፍ ያለው ትብብር በተቋም ግንባታ፣ ቴክኒክ ድጋፍ፣ በአካዳሚክ አቅም ልማት፣ በምርምር እና የተቋማዊ ለውጥ ላይ ያተኩረ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ትብብሩ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አካዳሚያዊ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ የትምህርት ጥራትንና ምርምርን ለማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቷን ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር በማሸጋገር ሂደት ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ ለዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ አመራር ልማት እና ለተቋማት አደረጃጀት የሰነድ ዝግጅት ድጋፍ ስታደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ፣ ጠንካራ እና ዘላቂ ሁሉን አቀፍ ትብብር አላቸው ብለዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት በትምህርት ዘርፍ ያላቸው አጋርነት የላቀ መሆኑን በማንሳት፤ የጆን ኤፍ ኬኔዲ ቤተ-መጽሐፍት አንዱ የትብብራቸው ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማህበረሰብ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለበርካታ ዓመታት ተማሪዎችን፣ ምሁራን እና ተመራማሪዎችን ሲያገለግል ቆይቷል ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግብርና፣ በህብረተሰብ ጤናና በሥራ ፈጠራ ዘርፎች የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውንና የጋራ የምርምር ፕሮጀክቶችን እየደገፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ራስ ገዝነት አስተዳደር በሚያደርጉት ሽግግር አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጀይሉ ዑመር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ታሪካዊውን የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ቤተ-መጽሐፍት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማክበር ትልቅ ክብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ቤተ-መጻሕፍት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት፣ የምርምርና የእውቀት ልውውጥ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
ቤተ መጻሕፍቱ ትውልድ ተኮር ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ተማሪዎችንና ምሁራንን በማፍራት የትምህርት ዕድገትና የባህል ጥበቃ መሰረት ሆኖ ማገልገሉን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፍ ያላቸውን የቆየ ተቋማትን የማጠናከር፣ የትምህርት ዕድል የማስፋትና የምርምር አጋርነት ያጠናክራልም ብለዋል፡፡