ከአረንጓዴ አሻራ እስከ ዓለም ገበያ - የኢትዮጵያ ቡና ልማት አዲስ የዕድገት ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
ከአረንጓዴ አሻራ እስከ ዓለም ገበያ - የኢትዮጵያ ቡና ልማት አዲስ የዕድገት ምዕራፍ
(በሙሴ መለሰ)
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመሆኗም ባለፈ ምርቱ አሁንም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ህይወት ትልቅ መሰረት ያለው ነው። የዓለም የቡና ዝርያዎች ሁሉ መገኛ የሆነው የአረቢካ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውም በኢትዮጵያ እንደሆነ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ቡና መጠጣት የዕለት ተዕለት ባህል ሲሆን፣ የቡና አፈላል ስነ ስርዓት ሰላምን፣ አንድነትንና ማህበራዊ ውይይትን የሚያጠናክር ትልቅ እሴት ተደርጎም ይወሰዳል።
በአሁኑ ወቅት ቡና ለሀገሪቱ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ ቀዳሚው የግብርና ምርት በመሆን ማዕከላዊ የኢኮኖሚ ሚናውን እየተጫወተ ይገኛል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ቡና የሚመረተው በተፈጥሯዊ መንገድ በገበሬዎች ማሳ ላይ ወይም በዱር ውስጥ በመሆኑ፣ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያና ኬሚካል ተጋላጭ አይደለም። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተመራጭነት ይበልጥ ከፍ አድርጎታል።
ከኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምሰሶ አንዱ የሆነው ቡናችን ለሀገሪቷ እያስገኘ ያለው ገቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም አንዱ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ቡና ነበር።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከብራዚልና ኮሎምቢያ በመቀጠል በዓለም 3ኛዋ ትልቋ የቡና ላኪ ሀገር መሆኗን እና በአፍሪካም ቀዳሚ ደረጃ ላይ መቀመጧን ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህ ውጤት ባለፉት 17 ዓመታት በድምሩ ከተገኘው 3 ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በዘርፉ የተመዘገበውን ከፍተኛ ዕድገት ያሳያል ብለዋል።
ለተመዘገበው ውጤት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም አጠናክራ መጠቀም እንዳለባት ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ የኢትዮጵያን የቡና ዘርፍ ከዘልማዳዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ ምርታማነት ለማሸጋገር የሚያስችል አዲስ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የተሻሻለ የልማት ፓኬጅ መዘጋጀቱን በቅርቡ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
ቡና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ የሚሊዮን አርሶ አደሮች የኑሮ መሠረትና የወጪ ንግድ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ታላቅ ሀብት በጥራትና በዘላቂነት በማሳደግ ከምርት ወደ እሴት፣ ከእሴት ወደ ዓለም ገበያ ማሸጋገር የዘርፉ ዋነኛ አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንኑ ስትራቴጂ ለማሳካት የተጀመረው ሃገራዊ የቡና ምርትና ምርታማነት ኢኒሼቲቭ በአሁኑ ወቅት በሔክታር 9 ኩንታል የሆነውን የቡና ምርታማነት ወደ 21 ኩንታል ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በ 1 ነጥብ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቡና ልማት ለማካሄድ የታቀደ ሲሆን፣ ለዚህም ምርጥ የቡና ዘር አጠቃቀም፣ የተቀናጀ የአፈር ንጥረ-ነገር፣ የቡና ተክል ጥግግት፣ የገረዛና የጥላ ዛፍ አያያዝ፣ የተቀናጀ የተባይ መከላከል፣ የመስኖ፣ የማዳበሪያ እንዲሁም የተሻሻለ የምርት አሰባሰብና የዕድሳት ሥራዎችን ያካተቱ ዘጠኝ የትኩረት መስኮች ተለይተው ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።
ይህ አዲሱ የቡና ልማት ኢኒሼቲቭ አርሶ አደሮችን፣ የማህበራትንና የባለሙያዎችን ግንዛቤና አቅም ለማሳደግ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎችን እንደሚከናውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ወጪ ንግድ ከአፍሪካ ቀዳሚና ከዓለም 3ኛዋ ትልቅ ላኪ ሀገር በመሆን ያሳየችው እመርታ፣ የዘርፉን ታላቅ የምጣኔ-ሀብት አቅም በተጨባጭ የሚያሳይ ነው። ለዚህ ደግሞ ላለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተፈጥሮን ምህዳር በማስተካከል ረገድ የራሱን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል።
በዚህም መርሃ-ግብሩ በተጀመረበት 2011 ዓ.ም 600 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተተከለው የቡና ችግኝ በየዓመቱ እያደገ በመሔድ በ2017 ዓ.ም ላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሸፈን ተችሏል።
ይሄ በመሆኑም የቡና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በ2011 ዓ.ም. ግማሽ ሚሊዮን ቶን የነበረው ዓመታዊ የቡና ምርት 2017 ዓም ላይ ወደ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ምርት ማግኘት በመቻሉ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማስቀጠል ችሏል።
በመሆኑም፣ የተያዘውን የተቀናጀ የልማት ስትራቴጂ በተግባር በመተርጎም የቡናን ምርት በጥራትና በብዛት ማሳደግ፣ የሀገሪቱን የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት ከመደገፍ ባለፈ የኢትዮጵያን ቡና የወደፊት ጉዞ እና ዓለም አቀፋዊ መሪነት እጅግ አስተማማኝ ያደርገዋል።