ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ዕድል መፍጠሩን ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈትኗት የቆዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ለመፍታት የሚያስችል እድል ተፈጥሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚችሉበትን ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ዋናው ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ ቆይቶ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተመካካሪ ቄስ ተሻለ አለባቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጉባኤው በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በስፋት እየመከረ ነው፡፡
በየደረጃው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የታደሙበት፣ የሀሳብ ብዝሃነት የሚስተናገድበት አካታችና አሳታፊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክክሩ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን የልዩነት ምንጭ ሆነው የዘለቁ አጀንዳዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረው ምክክር ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ ተሞክሮ እንደሚወሰድበት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በዓድዋና በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ የጻፍነውን አኩሪ ታሪክ በምክክሩ ላይ በመድገም ለትውልድ አሻራ አስቀምጠን እናልፋለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ተመካካሪ ድንቅነሽ ኡባራ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የየራሳቸውን ሀሳብ ማንጸባረቃቸውን ገልጸው፤ ጉባኤው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚቻል አመላክቷል ብለዋል፡፡
ጉባኤው ዜጎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር የሀገር ሁለንተናዊ ልማት እንቅፋቶችን በማለፍ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ የሚያስችል ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ ተመካካሪ አበራሽ አባይነህ ናቸው፡፡
ተመካካሪዎች መደማመጥን መርህ በማድረግ ለምክክር በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀሳቦችን መሰንዘራቸውን ገልጸው፤ ሀገርን የሚያጸና መፍትሔ እንደሚመጣ ተስፋ ሰንቄያለሁ ብለዋል፡፡