በክረምቱ ማጠቃለያ ወቅት የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለመቀነስ ያለመ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በክረምቱ ማጠቃለያ ወቅት የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለመቀነስ ያለመ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በክረምቱ ማጠቃለያ ወቅት የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለመቀነስ ያለመ የደም ልገሳ መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ሲሉ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር መላሽ ገላው ገለጹ።
ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ ዘመቻ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት እና በሙስሊም ተማሪዎች ሊግ (MS League) ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከነሐሴ 21 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ነው።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ የደም ለጋሾች ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር መላሽ ገላው ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ ዘመቻ አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ ዘመቻው የሚካሄድበት የነሐሴ መጨረሻ ወቅት የደም ክምችት የሚቀንስበት በመሆኑ መርሐ ግብሩ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል።
ስለሆነም ወጣቱም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ የደም ልገሳ ዘመቻ መርሐ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የሙስሊም ተማሪዎች ሊግ የዑምራ ሰብ-ቻፕተር አመራርና የደም ልገሳ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አክረም መሐመድ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለመቀነስ እና የእናቶች፣ የአደጋ ተጎጂዎችና የካንሰር ታካሚዎችን ሕይወት ለመታደግ ዘመቻው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በየዕለቱ ደም ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ለመድረስ ርብርብ በማድረግ የሚጠበቅብንን ለማበርከት ዘመቻው አስፈላጊ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
የደም ልገሳ ዘመቻ መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።