የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽነትና አካታችነት ለማረጋገጥ በማህበረሰብ ፍትህ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ስርዓቱን ተደራሽነትና አካታችነት ለማረጋገጥ በማህበረሰብ ፍትህ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የፍትህ ስርዓትን ተደራሽነትና አካታችነት ለማረጋገጥ ከመደበኛው ባለፈ በማህበረሰብ ፍትህ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለፀ።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር ያዘጋጀውን የኢትዮጵያ ቤተሰብ ፍትሕ መምሪያ ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ ቤተሰብ ፍትሕ መምሪያው ለቤተሰብ፣ ሕጻናትና ተጋላጭ ወገኖች የሕግ ጥበቃን ለማረጋገጥና ማህበራዊ ፍትሕን ለማስፈን የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
መምሪያው በቤተሰብ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱ የሕግ ጉዳዮችን በማስረጃና በተግባር ላይ በተመሠረተ አሠራር በመምራት መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የፍትህ ስርዓቱን በመደበኛውና ከመደበኛው ውጭ ተደራሽነትና አካታችነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።
የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ማጠናከርና ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፤ በዘጠኝ ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና አግኝተው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል በአራተኛ ደረጃ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው።
መምሪያውም በቀለብ፣ በልጆች አስተዳደግና ጉብኝት፣ በንብረት አስተዳደር፣ በፍቺና በንብረት ክፍፍል እንዲሁም ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ የሕግ ጉዳዮች ላይ የሚመራና የሚዳስስ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቤተሰብ፣ ሕጻናትና ተጋላጭ ወገኖች የሚደረገውን የሕግ ጥበቃ ለማረጋገጥና ማህበራዊ ፍትሕን ለማስፈንም መምሪያው ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቤተሰብ ፍትሕ መምሪያው ከዳኞች፣ ከትምህርት ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት በተውጣጡ ባለሙያዎች ኮሚቴ በማቋቋም የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል።
የመምሪያው ዝግጅት ሂደትም በማስረጃና በተግባር ላይ የተመሠረተ አሠራርን በመከተል መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ልዑል ካህሳይ በበኩላቸው፤ መምሪያው ባለሙያዎች የተቀራረበ የህግ አተረጓጎም እንዲኖራቸው በማድረግ ለፍርድ ቤቶች አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
የሄግ የሕግ ፈጠራ ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሼከር ፑላ በበኩላቸው፤ መምሪያው የማህበረሰብ ፍትህን በማስፋት ሰዎች በአቅራቢያቸው ፍትህን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።
መምሪያው መልካም ተሞክሮዎችን በማጋራት ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክርክሮችን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የመምሪያው የባለሙያ ኮሚቴ አባልና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ንጉሴ አፈሻ(ዶ/ር) ናቸው።