ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙሃንን አቅም ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የሚዲያ ሬጉላቶሪ ሥርዓትን ማጠናከር የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ ከተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚሁ ወቅት፤ መገናኛ ብዙሀን ለሀገር እና ትውልድ ግንባታ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዘመኑ ሀሰተኛ መረጃ በስፋት የሚስተዋልበት ጋዜጠኝነትና አክቲቪዝም የተደበላለቁበት መሆኑን ገልጸው፤ የዲጂታል ሚዲያውን አሉታዊ ተጽዕኖ መቆጣጠር የሚያስችል ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ብሔራዊ ጥቅም፣ የህዝብ ሰላም እና ደህንነት የመገናኛ ብዙሃን የስራዎቻቸው ማጠንጠኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህም ስርዓት መፍጠር እና ተሞክሮዎችን መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የሬጉላቶሪ ስራዎቹን በላቀ መንገድ ማከናወን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የመገናኛ ብዙሃን የአቅም ግንባታ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስተሳሰር ቅንጅታዊ አሰራር ለመዘርጋት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በተቋማት መካከል ፈጣን እና ዲጂታል የመረጃ ልውውጥ ስርዓትን በመዘርጋት ክፍተትን የሚያስወግድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት የተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ ናቸው።
የሀገረ መንግስት ግንባታውም ስሁት እይታን በሚያርም መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም ያለመገናኛ ብዙሀን ተሳትፎ ማሳካት እንደማይቻል ጠቁመዋል።
ስምምነቱ በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመው፤ የመረጃ ነጻነት አዋጅ የመረጃ ውስንነትን በጉልህ እንደሚፈታና ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችም ትልቅ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ስምምነቱን ካደረጉት ተቋማት መካከል የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሀላፊ ኮሎኔል ቢረሳው ሽፈራው ስምምነቱ ቅንጅታዊ አሰራርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ጊዜያትም በስምምነቱ መሰረት ስራዎች በላቀ መንገድ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አማካሪ ኮሚሽነር አሊ ዲኒ በበኩላቸው፤ ቅንጅታዊ አሰራሩ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ጊዜውን የጠበቀ እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የቅንጅት አሰራር እያደገ በሄደ ቁጥር የመቆጣጠር አቅም እየጨመረ እንደሚሄድ የገለጹት ደግሞ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።
ይህም በጉዳዩ ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።
የኢፌዲሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ መገናኛ ብዙሀን የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ በየጊዜው አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።