ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ የጋራ ውል

በሙሴ መለሰ

በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አሁን ላይ የሕዝቡን የጋራ እይታ ወደሚያንጸባርቁ ተጨባጭ የምክረ-ሃሳብ ሰነድ በመቀየር ላይ ይገኛል።
 
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለውና ነገ አንድ ወሩን የሚደፍነው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ፣ የልዩነቶችን በር እየዘጋ የጋራ ወደሆኑ መፍትሔዎች እየተሸጋገረ ይገኛል።
 
በጉባኤው ላይ ከሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የተወጣጡ 4ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፣ ይህም የውይይቱን አሳታፊነትና ህዝባዊ መሰረት በእጅጉ የሚያጎላ ነው።
 
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዋናው ጉባኤው የሚሆኑ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ በማድረግ ወደ ውይይት ተገብቷል።
 
እነዚህም አጀንዳዎች የሀገር ግንባታን፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽን፣ የፖለቲካና የምርጫ ሥርዓትን፣ የፌዴራል ከተሞች ጉዳይን፣ የሃይማኖት ጉዳዮችን፣ የተቋማት ግንባታን፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶችን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን፣ የሙስናና መልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲሁም የሰላም ግንባታን ያካተቱ ናቸው።

 
እያንዳንዱ አጀንዳ በ500 አባላት በተደራጁ ስምንት ልዩ የሥራ ቡድኖች ተከፍሎ ሲመካከርባቸው ቆይቷል።
 
ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ተከታታይ ውይይቶች ተሳታፊዎች እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ ልዩነቶችን በመሰብሰብ እና ወደ አማካይ ሃሳብ በመምጣት በኩል ትልቅ እርምጃ ማሳየት ችለዋል።
 
ተሳታፊዎቹ በመግባባት የተዘጋጁትን የተጠናከሩ  ምክረ-ሃሳቦች በመቀበልና የቃለ-ጉባኤ ሰነዶችን በመፈራረም ለወደፊቱ የሀገሪቱ አቅጣጫ መሠረት የሚሆን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።  
 
የሥራ ቡድኖቹ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራቸውን በማጠናቀቃቸው፣ አሁን ሂደቱ ወደ ሁለተኛውና ወሳኙ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
 
የተበታተኑትንና በተለያዩ ቡድኖች የቀረቡትን ምክረ-ሃሳቦች ወጥነት ባለው መልኩ ለማደራጀትና ለማጣጣም ስምንት ልዩ ቡድኖች ተዘጋጅተዋል።
 
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ የሂደቱ አጠቃላይ ሂደት ሦስት አራተኛ ያህል መጠናቀቁ ላለፉት ረጅም ጊዜያት ሲደከምበት የቆየው የሕዝብ ውይይትና ልፋት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ በቅርብ እንደሚሆን አመላካች ነው።
 
በሂደቱ ወቅት የሚነሱ ቅሬታዎችንና የተለያየ አስተያየት ያላቸውን ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳብ ለማስተናገድም ግልጽ የሆነ አሰራር የተቀረጸ ሲሆን፣ ይህም የውይይቱን ፍትሐዊነት የበለጠ ያጠናክረዋል።
 
በአጠቃላይ፣ የ4ሺህ የሕዝብ ወኪሎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉበት የሚገኘው ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።
 
የነገዋን ሀገር በጋራ መግባባት ላይ ለመገንባት የተጣለው መሠረትም ተጨባጭ ፍሬ የሚያፈራበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም