ቀጥታ፡

በክልሉ ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ለእንስሳት ጤና ትኩረት ተሰጥቷል

ጂንካ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ለእንስሳት ጤና ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ 

በክልሉ ዲመካ ከተማ ከ446 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚገነባው የዲመካ ክልላዊ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ለእንስሳት ጤና ትኩረት ተሰጥቷል፡፡


 

በክልሉ የእንስሳት እርባታ በተለይ የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት በመሆኑ የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የአርብቶ አደሩን ሕልውና መጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ዲመካ ላይ የሚገነባው የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ከአካባቢው አልፎ ለክልሉም ጥቅም የሚሰጥና ለእንስሳት ጤና መጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የላቦራቶሪ ፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር አደጋ ሥጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ስዩም መታፈሪያ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የዲመካ ክልላዊ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው።


 

ለግንባታው ከ446 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ጠቅሰው፣ ላቦራቶሪው በመንግሥት እና  በዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚገነባ አስታውቀዋል።

ግንባታውን በአንድ ዓመት ከ6 ወር ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸው፣ ላቦራቶሪው የእንስሳት በሽታ ምልክቶች ሲኖሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወዳሉ ሀገር አቀፍ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪዎች ናሙና በመላክ ሲባክን የነበረውን ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም