የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው
ባህርዳር፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ፡፡
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለ19 ሺህ 698 የከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ ቦታ ለመስጠት የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት አካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በስነ ስርአቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ዜጎችን የመኖሪያ የቤት ባለቤት የማድረግ ጉዳይ ከመንግስት የሰው ተኮር ፕሮጀክት አንዱ ነው።
የባህር ዳር ከተማን እድገት ለማፋጠን ከሚከናወነው የመሠረተ-ልማት ግንባታ ጎን ለጎን የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በ901 ማህበራት ለተደራጁ 19 ሺህ 698 ዜጎች የብሎክ ዕጣ ማውጣት መቻሉን አስታውቀዋል።
የብሎክ ዕጣ ማውጣት የተቻለው የከተማ አስተዳደሩ ለቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ አስፈላጊውን ካሳ በመክፈልና ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረጉ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም እስከ 10 ዓመት ድረስ ይቆይ የነበረውን የቤት መስሪያ ቦታ የማቅረብ ሂደት አሁን ላይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።
ይህም ዜጎች ተረጋግተው ተግባራቸውን እንዲከውኑ ለማድረግ ከማስቻሉም በላይ ከተማዋን ለኑሮ፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት የተመቸች ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
የቤት መስሪያ ቦታው የሚሰጠው በወረብ፣ በአዲስ ዓለም፣ በመኮድና በሰልቸል ሳይቶች መሆኑንም አብራርተዋል።
የቦታው ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች ፈጥነው ወደ ግንባታ በመግባት ለወጣቶች የሥራ ዕድል፣ ለራሳቸውም ሀብት እንዲፈጥሩ አቶ ጎሹ አሳስበዋል።
በዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ፣ የክልሉ ባለድርሻ አካላት እና የማህበራት ተጠቃሚ አባላት ተገኝተዋል።